You are here: HomeNews/Events“አደይ አበባ ግንቦት ላይ ብትወጣ ማን ዞሮ ያያታል?”

“አደይ አበባ ግንቦት ላይ ብትወጣ ማን ዞሮ ያያታል?”

Published in News and Events Monday, 26 June 2017 09:14

አስቴር አበበ በቅርቡ ያወጣችው የመዝሙር ሰንዱቅ (አልበም) በስፋት እየተደመጠ ነው። በርካቶችም እጅግ እንደ ወደዱት ይናገራሉ። ለመሆኑ አስቴር ማናት? የት ነው የምትኖረው? ወደ ኢትዮጵያ ለምን አትመጣም? በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከጳውሎስ ፈቃዱ ጋር በስልክ ያደረጉት ውይይት እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

ጥያቄ፡- እኔን እና አልበምሽን ካስተዋወቀን ነገር ልጀምር። ይኸውም “ክብር የበቃህ ነህ” የሚለው የመዝሙርሽ ርእስ ግራ አጋቢነት ነው። ለምን ይህን ርእስ መረጥሽ?

አስቴር፡- “ቀድሞም” የሚለውን ቃል ከፊት ባስገባበትና “ቀድሞም ክብር የበቃህ ነህ” የሚል ባደርገው ስለሚረዝም ነው አሳጥሬ ያቀረብኩት እንጂ ማንም ላይ ጥያቄ ይፈጥራል ብዬ አስቤ አልነበረም።

 

ጥያቄ፡- ዝማሬ እንዴት ጀመርሽ?

መልስ፡- የሰባት፣ የስምንት ወይም የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ላይ ሆኜ፣ ግድግዳ ላይ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየገጣጠምኩኝ ለእናቴ ስዘምርላት አስታውሳለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ የዝማሬ ጸጋ ውስጤ እንዳለ የነገረችኝም እርሷ ናት። በአንድ አገልጋይ በኩል ጌታ ነገራትና ያንን ሁሌ ትነግረኝ ነበር። እንግዲህ ዘማሪ እንድሆን የእግዚአብሔርም ዕቅድ ነበረ ማለት ነው። ያ ነው እንግዲህ እያደገ እያደገ እዚህ ጋ የደረሰው።

 

ጥያቄ፡- በምን ዐይነት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሽው? አንቺስ ምን ዐይነት ቤተሰብ መሠረትሽ? እስቲ ስለ ኑሮሽ፣ ቤተ ሰብሽና ሥራሽ አጫውቺኝ።

አስቴር፡- በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት። ባለቤቴ በጌታ ነው። ሦስት ቆንጆ ሴቶች ልጆች አሉኝ። ጥሩ ትዳር አለኝ። እግዚአብሔር ይመስገን። በጣም የሚደግፈኝ፣ በውስጤ እግዚአብሔር ላስቀመጠው ነገር ዋጋ የሚከፍል ባል ነው እግዚአብሔር የሰጠኝ።  

 

ጥያቄ፡- ስም አለው አይደል?

አስቴር፡- ማን? ባለቤቴ?

 

ጥያቄ፡- አዎን።

አስቴር፡- እንዴ አዎ! ሽፌ። ሽፈራው። (ሣቅ)

 

ጥያቄ፡- ሙሉ ስሙ?

አስቴር፡- ሽፈራው ዘውዴ ገበየሁ።

 

ጥያቄ፡- ዝማሬዎችሽን በዚህ ጊዜ ለማሳተም እንዴት ወሰንሽ? ምን ያህልስ ጊዜስ ወሰደብሽ?

አስቴር፡- እንግዲህ እንደ ማንኛውም ዘማሪ ዕድሎችን ሳልጠቀም ቀርቼ አይደለም። ሞክሬአለሁኝ። ግን አሁን በዚህኛው ጊዜ ላይ ዴቭ [ዳዊት ጌታቸው] ወደዚህ እንደሚመጣ ሳስብ፣ እንዲያናግርልኝ ካናዳ ለሚገኘው ዘማሪ ለግሩም ታደሰ ነገርኩት። ፓስተር ዘርዬ [ዘሪሁን ኀ/ሚካኤል] አናገረልኝ። ከዚያም እርግጡን ሳውቅ ለዴቭ ራሴ ደወልኩለት። እርሱም ዘማሪ ነው። በብዙ ፍርሃት ነው ያናገርኩት። እንዲሁ በቀላሉ ልጠይቀው አልደፈርኩም። በእርግጥ “ልጸልይበት” ብሎኝ ጥቂት ቀናትን ወስዷል። ከዚያ ግን አዎንታዊ መልስ ነው የሰጠኝ። እግዚአብሔር ይባርከው! በቃ መዝሙሩን ለመሥራት ጊዜው ሆነ!

 

ጥያቄ፡- የመዝሙር ቀረጻው በአንድ ሳምነት ነው ያለቀው ልበል?

አስቴር፡- አዎ። ከተነጋገርንበት ጊዜ አንሥቶ አንድ ሳምንት ነው። ግን ስቱዲዮ ተገብቶ የድምፅ ዳታውን መውሰዱ በሁለት ቀን ውስጥ ነው ያለቀው። በመጀመሪያ ቀን ወደ ስድስት አካባቢ ዝማሬዎችን፣ በሚቀጥለው ቀን ደሞ የቀሩትን ዝማሬዎች ወሰድን።

 

ጥያቄ፡- እርጉዝ ነበርሽ ያኔ መሰለኝ?

አስቴር፡- አዎን የሰባት ወር እርጉዝ ነበርኩኝ። ከድካም ጋር …

 

ጥያቄ፡- የእርጉዝ ድምፅ ነዋ የምንሰማው!

አስቴር፡- ምን ሰምተህ ነው? የሁለት ሰው ድምፅ ሰማህ?

 

ጥያቄ፡- ሙዚቃው በስንት ጊዜ ተሠርቶ አለቀ?

አስቴር፡- ሦስተኛ ልጄን ወልጄ አራተኛው ወር ላይ “ጨርሼዋለሁ ውሰጂ” ሲለኝ አስታውሳለሁ። ግን እንዲቆይ ፈለግሁ። ፈጠነብኝ። ወጥቶ ይደመጣል ወይ? በእኔ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንደ ፈጠረ፣ ወጥቶስ በሰው ሕይወት ላይ ይህንን ይፈጥራል ወይ? የሚለው ፍርሃቱም አለ። ከጊዜ አንጻር ነው የማወራህ። ጊዜ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። እግዚአብሔር እንድንሠራለት የሚፈልገው ነገር አለ። ያ ነገር ደሞ የሚሆንበት ጊዜ አለ። “አሁን በቃ ይሆናል! ይሳካል!” እንደዚህ አይነት ነገር አልልም እኔ።

ለምሳሌ አሁን እግዚአብሔር ሰሞኑን እያስተማረኝ ያለው ነገር አለ። አደይ አበባ አሁን ያለሁበት አገር ምንም ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ ግን አደይ አበባ የምትወጣው አሁን መስከረም ላይ ነው። የአዲስ ዓመት መምጫ ምልክት ናት። የመስቀል ዕለት ሰዎች ከሳር ጋር ቤታቸው ይጎዘጉዟታል። የአደይ አበባ መድመቋ ጊዜዋን ጠብቃ በመስከረም መውጣቷ ስለሆነ ነው። በሰዎችም ዘንድ ተፈላጊነቷ ይኸው ነው። ልጆች እያለን፣ ፈልገን እንድናመጣ ተልከን፣ እባብ ምናምን ያለበት ሩቅ ገደል ውስጥ ድረስ ገብተን አደይ አበባ ቀጥፈን ስናመጣ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ያ ሁሉ ዋጋ የሚከፈለው ወቅቷ ስለሆነ ነው። ሌላ ጊዜ ማንም እንደዚያ አይሆንላትም። አደይ አበባ ግንቦት ላይ ብትወጣ ማን ዞሮ ያያታል? ማንም! አሁን አሁን በኢትዮጵያ ያን ዐይነት ነገር ነው ሰዉ አእምሮ ውስጥ ያለው። ስለዚህ እግዚአብሔርም ሰውን የሚያወጣበት ወቅት አለው። የእግዚአብሔርን ጊዜ አለማወቅ ለኪሳራ ይዳርግሃል! እኔም ጌታን ቀድሜው ከስሬም አውቃለሁ። ዝማሬዎችን ልኬ፣ ስንትና ስንት ነገር አድርጌ፣ ምንም ምንም ሆኖ የቀረበት ሁኔታ አለ። ከሰዎች ክፋት እኮ አይደለም። ግን እኔ ወቅቴ ስላልሆነ ነው። እኔንም ሲያስጨንቀኝ የነበረው ይኸው ነበር፤ ጊዜው ነው ወይ? የሚለው ነገር!

 

ጥያቄ፡- መዝሙርሽ ይህን ያህል ተቀባይነት እንደሚያገኝ ገምተሽ ነበር? ተቀባይነቱን ስታውቂ ምን ተሰማሽ?

አስቴር፡- እንዲህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅሁም። በፍጹም። በጣም ነው የደነገጥኩት። ጌታንም አመስግኛለሁ በጣም። በቃ ደስ ነው ያለኝ። ምክንያቱም ከደወሉልኝ ሰዎች መካከል፣ ከጻፉልኝ ሰዎች መካከል ከጌታ ቤት የወጣ ልጅ፣ በእናቷ ሞት ሐዘን ውስጥ የነበረች ልጅ … ሁሉ አሉበት። አንዳንዶቹ ደሞ “ማን ነው የነገረሽ? ስለ እኔ ነው የዘመርሺው” ብለውኛል።

 

በመጀመሪያ ደረጃ ዝማሬዎቹን የዘመርኳቸው ሲዲ ለማውጣት ሳስብ አይደለም። በጣም ረጅም ጊዜ የቆዩ ዝማሬዎች አሉበት። ስምንት ዓመት፣ ዐሥር ዓመት ሁሉ የቆየ ዝማሬ እዚያ ውስጥ አለ። ለሲዲ ብዬ የሠራኋቸው ዝማሬዎች አይደሉም። ከጌታ ጋር የማወራባቸው፣ በጸሎት ሰዓት ላይ የምነጋገርባቸው ናቸው። መዝሙሮቹ ላይ ያሉ ስሜቶች በሙሉ የነኩኝ ናቸው። እኔን ነክተውኛልና ከሕይወቴ የወጡ ናቸውና ሲዲው ሲወጣ ደሞ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ፈጠረ።

 

ጥያቄ፡- ስጦታ ይጎርፍልሻል አሉ!

አስቴር፡- አዎን፣ “ጌታ ይባርክሽ! ያሳድግሽ! ያብዛልሽ! አትውረጂ!” የሚሉ የቃላት ስጦታዎች ይጎርፉልኛል። ያው በእጄ የገባ ባይሆንም፣ ከዚህ በላይ ምንም ስጦታ የለም።

 

ጥያቄ፡- አልበምሽ እንዲህ ተቀባይነት ባገኘበት ጊዜ አገር ውስጥ ያለ መኖርሽ ጎድቶሻል? ለምሳሌ ከአገልግሎት አንጻር?

አስቴር፡- ትክክለኛውን ነገር ነው የምነግረህ። ከእግዚአብሔር ሐሳብ ያመለጠ፣ ከፈቃዱ ምክር ውጭ የሆነ ነገር በሕይወቴ ላይ እንደማይደርስ ነው የማውቀው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በድካም ምክንያት፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ባለመስማት ምክንያት በሕይወታችን ላይ የሚደርሱ ነገሮች ይኖራሉ። ሆኖም እነዚያን እንኳን ታግሦ ወደፊት የሚያስኬድ አምላክ እንዳለኝ ነው እኔ የማውቀው። ከዚያ አንጻር አሁን ለእኔ ሲዲው ምንም ያህል እየተሰማ ይሁን፣ ሰዎችም በአካል ተገኝቼ እንዳገለግልባቸው የሚናፍቋቸውና እኔም ሄጄ ባገለግልባቸው የምናፍቃቸው መድረኮች ይኑሩ፣ እግዚአብሔር ፍቃዱ ስለሆነ ነው እዚህ ምድር ላይ ያለሁት።

 

ከአገልግሎትም ባለፈ ቤተ ሰቤን እናፍቃለሁ፤ ለዐሥር ዓመት እናቴን አላየኋትም። በዚህ ናፍቆት ውስጥ ሆኜ የምነግርህ፣ አሁንም ቢሆን የማንም ግፊት ስቦኝ የሆነ ቦታ መሄድ አልፈልግም። ማንም እንደማያስቀረኝ ግን ዐውቃለሁ። ሰዎች እዚህ ምድር ላይ ብዙ ስለ ቆየሁኝና እየወጣሁ እንዳገለግል ከመናፈቃቸው የተነሣ፣ “እንዲህ ብትሆኚ፣ ይህንን ብታደርጊ፣ ወረቀትሽ እንዲህ ቢደረግ፣ እንዲህ ቢሆን ኖሮ …” የሚሉት ነገር አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ያቀደው ነገር ብቻ ነው በሕይወቴ የሚሆነው። ሁሌም ቢሆን ናፍቆቴ ጌታን ቀድሜ አለመሄድን ነው። ከጌታ ፍቃድ፣ እግዚአብሔር ሊያደርግ ካለው ነገር ዐልፌ መሄድን አልፈልግም። በቃ ... “እንደዚህ አይነት ሴት ነኝ” እያልኩ ሳይሆን፣ ሁሌም ቢሆን ወደ ኋላ ብቀርበት፣ ዐቅፎ በሚፈልገው ፍጥነት የሚያስኬድ አባት ስላለኝ ነው ይህን የምልህ። ሁሌም ቢሆን የጌታ ፍቀድ በሕይወቴ እንዲሆንልኝ ነውና የምፈልገው፣ ከዚያ አንጻር ይሄ ትክክለኛ ቦታዬ ነው ብዬ ነው የምለው።

 

ይህንን በምሳሌ ላስረዳህ። አሁን አንተ ልጆች አሉህ። ከልጆችህ ጋር መንገድ እየሄድክ ነው እንበል። ልጆችህ በመንገዱ ርዝመት ደክሟቸው ሊሆን ይችላል። ወደ ኋላ ሲቀሩብህ ምንድን ነው የምታደርገው? የደከሙትን ዕቅፍ አድርገህ፣ አንተ በምትሄድበት ፍጥነት ነው ወደፊት የምታስኬዳቸው። የእኔ እግዚአብሔር ደግሞ ከዚህ የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ ሰዎች ሲዘገዩ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ በሚገርም ፍጥነት ያስኬዳቸዋል። መርዶክዮስን፣ ኤልያስን … መጥቀስ እችላለሁ። አሁን ያለሁበት ቦታ ትክክለኛ ቦታዬ ነው። ጊዜው ሲደርስ ወይ አገር ቤት፣ ወይ አንዱ ቦታ ይወስደኛል። ምን ልልህ ፈልጌ ነው? የእግዚአብሔር ነገር፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ የፈቃዱ ምክር በሕይወቴ ላይ ይሆን ዘንድ የሁሌም ናፍቆቴ ነው። ነገር ግን እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያውቃል። እና ምንም ጸጸት የለም ውስጤ። “እንዲህ ብሆን፣ ኢትዮጵያ ብሆን ኖሮ …” የምለው፣ ወይም አቋራጮችን ልፈልግ የምሯሯጥበት ምንም ዐይነት ነገር የለም። ባማረ በደመቀ ሁኔታ ነገሮቼ በጊዜው እንደሚስተካከሉ አምናለሁ።

 

ጥያቄ፡- ግጥሞቹና ዜማዎቹ በሙሉ የአንቺ ናቸው?

አስቴር፡- ግጥሞቹም ዝማሬዎቹም የእኔ ናቸው፤ ከጌታ የተቀበልኳቸው።

 

ጥያቄ፡- መዝሙር ተሰርቆብሽ ያውቃል?

አስቴር፡- መዝሙር ተሰርቆብኝ አያውቅም፤ ተወስዶብኝ ያውቃል።

 

ጥያቄ፡- ምን ማለት ነው?

አስቴር፡- መሠረቅ ማለት አንተ ጋ መኖሩን እያወቅኸው በሆነ መንገድ ከእጅህ የወጣ ነገር ነው። ይህኛው ግን የተለየ ነው። ሰዎች እንዲሰሙት ወይም ስለ ወደዱት መድረክ ላይ እንዲያገለግሉበት በፈቃዴ የምልካቸው ዝማሬዎች አሉ። ለምቀርባቸው ለጓደኞቼ “ዝማሬ ተቀበልኩ” ብዬ መላክ ያረካኛል። ዝማሬን ከተቀበልኩ በኋላ እኔው ጋ ሳቆየው ደስ አይለኝም።

 

ጥያቄ፡- እንዲያሳትሙት ነው የምትልኪው?

አስቴር፡- No! እንዲሰሙት። እንዲሰሙት ነው የምልከው።

 

ጥያቄ፡- ግን ያለ ፈቃድሽ ያሳተሙ የሉም?

አስቴር፡- አሉ። እንደዚያ ሆኖብኝ ያውቃል።

 

ጥያቄ፡- ታዲያ አገልግሎቱ በአንዳንድ ሰዎች ምክንያት እንዲህ እየወረደ በመሆኑ ምን ይሰማሻል?

አስቴር፡- አገልግሎቱ የወረደ ሆኖ አይደለም። ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ፣ ክርስቶስን የምትመስል ቤተ ከርስቲያን ለመፍጠር … እግዚአብሔር ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ዝማሬ ነው። ግን አሁን ባለቤቱ ይወስነዋል፤ ነገርየውን ለማክበርም ለማቅለልም ማለት ነው። እና ከዚያ አንጻር እንግዲህ ያ ሰው ነው ወሳኙ።

 

ጥያቄ፡- የመዝሙር አልበሙን በሚመለከት “እንዲህ ባደረግሁት ኖሮ!” ብለሽ የሚቆጭሽ ነገር አለ?

አስቴር፡- ሙዚቃው ላይ ምንም ዐይነት ጥያቄ የለኝም። ግን ከግጥም አንጻር፣ ከመንፈሳዊ ልጅነት አንጻር፣ አንዳንድ መግባት የሌለባቸውን ቃላት፣ መሆን የማይገባቸውን አባባሎች ተጠቅሜአለሁ። ከእነዚያ አንጻር ሳየው፣ ፌስቡክ ላይ ጠቅሰሃቸው እንደዚያ ሳልቀጠቀጥ “ምነው ለአንተ ባሳይህ ኖሮ!” ብያለሁ። (ሣቅ)

 

ጥያቄ፡- “ትልቅ የሆነውን” በሚለው የአልበምሽ የመጀመሪያ መዝሙር ላይ “ሁሌ ብቻውን የሚመለክ ትልቅ፣ የሚጨምር ክብር ከትናንቱ ይልቅ” ትያለሽ። ይህንን ፌስቡክም ላይ አቅርቤው ነበር። ለመሆኑ እግዚአብሔር ከትናንት ወደ ዛሬ የሚጨምር ክብር አለው?

አስቴር፡- እግዚአብሔር በየዕለቱ የማይጨምር ማንነት አለው። የማይቀንስ ማንነት አለው። “ክበር” ተብሎ የማይከብር፣ ሰዎችም “አትክበር” እንኳ ቢሉት እርሱ ራሱ ራሱ ነው። በቃ! የማይጨምር የማይቀንስ ማንነት ነው ያለው። እኔ በተጠጋሁት ቁጥር፣ የእኔ እርሱን ማወቅ ነው ዕለት ተዕለት እየጨመረ፣ እየተጨመረ የሚሄደው። እኔ እርሱን በተጠጋሁት ቁጥር፣ እኔ እርሱን ባወቅሁት ቁጥር፣ የእኔ ዕውቀት መጨመሩን፣ በሕይወቴ ላይም ሆነ በሰዎች ሕይወት ላይ እንደዚያ ሲጨምር ማየቴን ለመናገር ፈልጌ ነው እንጂ የእርሱ ማንነት የሚጨምር ሆኖ አይደለም። የእኔን የመጠጋት ልክ ለማሳየት ነው።

 

በዚሁ መዝሙር ላይም፣ “እርሱ፣ እርሱ” እያልሽ የምታልፊያቸው ሁለት የተለያዩ አካላት አሉ። ማን ማን እንደ ሆነ አይታወቅም። የመጀመሪያው፣ “ከፍታውን ተመኝቶ ከፍ ብያለሁ ያለ፣ ላፍታ ማን ተመቸው ማን ተደላደለ፣ ወርዷል ወደ ቦታው እርሱ ወዳዘዘለት፣ ልክን ማወቅ እያለ ኋላ ከመዋረድ” የሚለው ነው። ከፍታውን የተመኘው ማነው? እንዲወርድ ያዘዘውስ ማነው? የሚቀጥለው ደግሞ፣ “ደጋግሞ ቢፎክር ቢጨምር ቀረርቶ፣ ልኩን አግብቶታል ከሰማያት ወርዶ፣ ዝቅ ብሎ ያለ ልክ ታዞ በመስቀል ላይ፣ የአብን ጥም አርክቷል ሆኗል ለዓለም ሲሳይ” የሚል አገላለጽ አለ። ይህም ማን እንደ ፎከረ፣ ማንስ ልክ እንዳገባው የማይገልጥ ድፍን አገላለጥ ነው! የፎከረውም፣ ልክ ያገባውም “እርሱ” ተብለው ነው የቀረቡት። ይህ ግርታ ይፈጥራል። ለምን እንዲህ አደረግሽ?

 

ልክ ነህ። ለምሳሌ ሁለተኛውን፣ “ጠላቴ ቢፎክር ቢጨምር ቀረርቶ፣ ልኩን አግብቶታል ጌታ ከላይ ወርዶ” እያልኩ መዘመር እችል ነበር። አሁን መድረክ ላይ እያረምኩ ነው የምዘምረው። መዝሙሩ ተሠርቶ ማለቁን ሳውቅ ደንግጫለሁ ብዬህ የለ? አንዱ ምክንያት እኮ ግጥሞቹ ያልታዩ በመሆናቸው ነው። ለማሳየት ያሰብኩት ለፓስተር ኤልያስ ግርማ ነበር። ከሥራ ጋር አልተመቻቸልኝም። ያለንበት አገር ሥራ የሚበዛበት ነው። በጊዜው ደግሞ እርግዝና ላይ ነበርኩ። ያ ባለመሆኑ ፍርሃት ነበረኝ። እንዲያውም ሲዲው ከመውጣቱ በፊት፣ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲዲ አዘጋጅቻለሁ። የቃላትም የሐሳብም ግድፈት ቢኖር ጉድለቱን ሞልታችሁ ስሙልኝ” የሚል መልእክት በፌስቡክ ላስተላልፍ ሁሉ አስቤ ነበር። ወዲያው ግን፣ “ክብር የበቃህ ነህ” የሚለውን ርእስ አንተ ፌስቡክ ላይ ለውይይት ስታቀርበው ደነገጥኩ። “ገና ከአሁኑ እንደዚህ ከሆነ፣ ዝማሬው ውስጥ ሲገባ ብዙ ስሕተቶችን ያገኛል” ብዬ ብዙ ተሰምቶኝ ነበር። “ጌታ ሆይ፤ ያለሁበትን ሁኔታ አንተ ታውቃለህ፤ እባክህን የሰውን ልብ ጠብቅልኝ” ብዬ እስክጸልይ ነው የደረስኩት። ልጅ እስኪያድግ ድረስ ከልጅነት የመነጩ አገላለጦች ይኖሩታል። ይህ ግን በማደግ ይሻራል። እናም ከዚህ በኋላ አይደገምም። ነገ ገና እግዚአብሔር በእኔ የሚያደርገው ነገር አለ ስል አስባለሁ። መኖሬ በራሱ ለዚህ ምስክር ነው። እናም ከልጅነት የወጡ አገላለጦችን በሙሉ እየተውኩኝ እዘምራለሁ። በጣም አመሰግናለሁ።

 

ጥያቄ፡- ንቴ ይመስክር” ብለሽ ትዘምሪያለሽ፤ ትናንትሽ ምን ይመስል ነበር?

አስቴር፡- ወላጆቼ ከተለያዩ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። ወደ 85 ዓ.ም ላይ ነው የተለያዩት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ዐልፌአለሁ። ያውም በልጅነት! ጠላት ሙሴን ለመግደል ሲፈልግ፣ አንድ ሙሴ የሚባልን ሕፃን ልጅ ለመግደል አልነበረም ዓላማው። እስራኤልን ነው ያየው። ሄሮድስ ኢየሱስን ለማጥፋት፣ ሕፃናትን ለማስገደል የፈለገው፣ መቼም እኛም ታይተን ነው ማለት ነው። እና ከዚያ አንጻር ዛሬዬን፣ ማለትም ነገ ላይ እግዚአብሔር በሕይወቴ ሊገልጥ ያሰበውን ነገር ጠላት ተመልክቶ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ዐልፌአለሁ። በራብ ውስጥ ዐልፌአለሁ። በመታረዝ ውስጥ ዐልፌአለሁ። የቤተሰብን ፍቅር በማጣት፣ በሰዎች በመገፋት ሁሉ ዐልፌአለሁ። ይህም እኔን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ ወንድሞቼና እኅቶቼም ያለፉበት ጎዳና ነው …።

 

ዛሬዬን ዐይቶ ሰልፌን የተሰለፈልኝ፣ እነዚያን ሁሉ ነገሮች ያሳለፈኝ፣ የሚደግፉ ሰዎችንና የሚያጎርሱ እጆችን ወደ ቤቴ የላከልኝ እግዚአብሔር ነው። ዛሬ ላይ ቢሆን ይሄን አላወራም። “እርቦኝ ነበር ትናንት” አልልህም። ምክንያቱም ከዚያ ደረጃ ያለፈ ነገር ነው። ግን ያኔ በወጣትነትም ሳይሆን፣ ገና ልጅ እያለሁ ነው የደረሰብኝ። ያኔ ለእኔ ቁምነገር መብላት መጠጣት ሊሆን ይችላል። ያኔ ለእኔ ቁምነገር እንደ ጓደኞቼ መልበስ፣ ቆንጆ ጫማ ማድረግ፣ ጥሩ ትምህርት ቤት መማር፣ እና እንደዚያ ዐይነት ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚያን ሁሉ ስሜቶቼን፣ እነዚያን ሁሉ ፍላጎቶቼን በቃ … ገርቶልኝ፣ ሰልፌን ተሰልፎልኝ ነው እዚህ ጋ የደረስኩትና … ለማለት አይደለም ያልኩት። እውነትም እግዚአብሔር ተዋግቶልኛል።

 

ጥያቄ፡- “የበረሃ ጓዴ” ስትዪስ? ወደ ደቡብ አፍሪካ በበረሃ አቆራርጠሽ ነው የደረስሽው እንዴ?

አስቴር፡- በበረሃ አቆራርጬ አልመጣሁም። በነገራችን ላይ፣ በበረሃ መምጣት እዚህ የተለመደ ነው። እስከ ቦትስዋና በአውሮፕላን መጣሁ። የተወሰነ ጊዜ እዚያ ቆየሁኝና ፖስታ በሚያመላልስ የDHL መኪና ነው አቆራርጬ እዚህ የደረስኩት። አሁን ግን መንገዱ በጣም ጥብቅ ስለሆነ፣ አንባብያን ይህንን መሞከር የለባቸውም። የእኔ ጊዜ ጥሩ ጊዜ ነበር። በነገራችን ላይ፣ እኔ ቀለበት አስሮልኝ ወደዚህ የመጣውን የዛሬውን ባለቤቴን ብዬ ነው የመጣሁት።

 

ጥያቄ፡- አሁንስ ከበረሃ ወጥተሻል?

አስቴር፡- ምን ያልቃል! ወደ ጌታ ስሄድ፣ ወይም እርሱ ሲመጣ ነው እንግዲህ በረሃው የሚያቆመው!

 

ጥያቄ፡- ልክ ብለሻል። እዚህ በአውሮፓ ያሉ አማኞችም ያሉበትን ስፍራ “ምድረ በዳ” በማለት ሲገልጹት መጀመሪያ እጅግ ተገርሜ ነበር።

አስቴር፡- ሁሉም ቦታ ምድረ በዳ ነው።

 

ጥያቄ፡- “ይሆንልኛል፤ ይሳካልኛል” የሚለው ፉከራሽ ከየት የመጣ ነው? ያውም “በቀራንዮ ተራራ ላይ ተፈጽሟል የእኔ ጉዳይ” ነው የምትዪው። የጌታ የመስቀል ሞት፣ በሞቱ ያገኘነው መዳን ከስኬት ጋር የግድ ይቆራኛል?

አስቴር፡- በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዝማሬው ራሱ ስለ ኑሮ ብልጽግና፣ ስለ ኑሮ ከፍታ አይደለም። በፍጹም! እኔ ከአሁን በኋላም ቢሆን ስለ ምድራዊ ብልጽግና አልዘምርም። ያ ዝማሬ ከምን አንጻር እንደሆነ ልንገርህ። በነገራችን ላይ እዚህ አሁን የኖርኩበት አገር ላይ ሦስት ጊዜ የመኪና አደጋ ገጥሞኛል። እና የመጨረሻው አደጋ ከመድረሱ በፊት ረቡዕ ዕለት በአንድ ስፍራ አገለገልኩኝ። ጠላት በፊቴ ያዘጋጀው የሞት ጎዳና መኖሩን፣ ግን ያንን ዐልፌ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልኝ ነገር እንደምገባ እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ በነበረው አገልጋይ በኩል ሲናገረኝ ነበር። ረቡዕ አገልግዬ ሐሙስ ዕለት ማታ ላይ ፕሪቶሪያ ከሚባል አገር ወደምኖርበት ጆሀንስበርግ እየመጣሁ እያለ በጣም የሚያስጠላ አደጋ ነው የደረሰብኝ። ግን ያለ ምንም ጭረት ነው ከዚያ ውስጥ የወጣሁት።

 

እናም እንደዚህ ዐይነት ነገሮች ሲደራረቡ አንዴ ምን እንዳደረግሁኝ ልንገርህ። ዝማሬዎቹን በማስተካከል እና በማረም፣ ያለቁ ዝማሬዎችን በሌላ ደብተር ላይ መገልበጥ ጀመርኩኝ። እነዚህን ዝማሬዎች ሊያቀርብልኝ የሚችለው ማነው? ስል ማሰብ ጀመርኩ። ምክንያቱም ጌታ ሊሰበስበኝ መሰለኝ። “ማገልገሉ ቢቀርስ? ከአንዴም ሦስት ጊዜ ነው እግዚአብሔር ያሳየሽ። እና ዐርፈሽ ተቀመጪ!” የሚል ድምፅ ከአሕዛብም ይቀርብልኝ ነበር። እኔም በቃ ፈራሁ። “እግዚአብሔር ምናልባት መዝሙሮችን እንድቀበልና በዚህች ምድር መድረኮች ላይ እንዳገለግል ብቻ ሊሆን ይችላል ፍቃዱ። መዝሙሮቹን ሌላ ሰው በሲዲ ያወጣቸዋል” የሚል ነገር ሁሉ ከአንደበቴ ወጥቶ ያውቃል። ገባህ አይደል? ስለዚህ “አይሆንም!” ለሚለው ለዚህ ዐይነቱ የጠላት ድምፅ፣ የሚያስፈልገው እንዲህ ዐይነቱ የፉከራ ድምፅ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። እንጂ ስለ ብር፣ ስለ ብልጽግና ምናምን ልዘምር ፈልጌ አይደለም። የሚገርምህ ነገር በዚህ ዝማሬ ብዙ ነገሮችን ተወጥቻለሁ። እንደገና ማንሰራራት ሆኖልኛል። በጣም!

 

ጥያቄ፡- ከአገልግሎትሽ ጋር በተያያዘ ተስፋ ቆርጠሸ ታውቂያለሻ?

የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ የሆነውን ልንገርህ። ተስፋ ቆርጬ የነበረበት ጊዜ ነበር። ሞክሬ ሞክሬ የደከመኝ ጊዜ ነበር። ያን ሰሞን በጌታ ፊት ሆኜ፣ “የትኛው ትውልድ እንዲሰማው ነው እነዚህን ዝማሬዎች የሰጠኸኝ?” እያልኩ ስጠይቅ ነበር። መዘመር የጀመርኩት ልጅ ሆኜ ስለሆነ መልእክቶቹ የሚያረጁ መሰለኝ። የቆዩ ዝማሬዎች ነበሩኝ። የእኔም ዕድሜ እየሄደ ነው። ቅድምም እንዳልኩህ፣ ሌሎች አማራጮችን የማፈላለግ ሙከራ አድርጌአለሁ፤ መዝሙሮቹን ሌላ ሰው እንዲዘምራቸው። እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ነገር የጨረሰ እስኪመስለኝ ደርሻለሁ።

 

በዚህ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እያለሁ ፓስተር ሚኪ [ሚካኤል ወንድሙ] ከአዲስ አበባ መጣ፤ ለአገልግሎት የጋበዘው ፓስተር ኤልያስ ነው። እናም በዚያ ወቅት እግዚአብሔር በሚኪ በኩል ተናገረኝ። ለግሌ የመጣልኝ መልእክት ከዮሴፍ ጋር የተያያዘ ነበር። ዮሴፍ ሰባቱ የረሃብ ዓመታት ከመምጣታቸው በፊት በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ውስጥ እህልን ሰበሰበ። ያ እህል ተከማችቶ ሰባት የጥጋብ ዘመናትን አሳለፈ። ከዚያ ሰባቱ የረሃብ ዘመንም ሲመጣ ያ እህል አላረጀም። አልሻገተም። ነቀዝ አልበላውም። ጌታ የተናገረኝ ዝማሬዬ ልክ እንደ ዮሴፍ እህል እንደሚሆን ነው፤ ሁሉም ሰው የሚበላው። ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚደመጥ። ካሴቱ ሲወጣም እንደዚያ ሆነ። ጌታ እንደ ተናገረኝ ነው ያደረገው።

 

እግዚአብሔር በሚኪ በኩል የተናገረኝ ነገር ስንቅ ሆኖኛል። ልብን በሚያሳርፍ ሁኔታ፣ በሚያረጋጋ ሁኔታ ቃል በቃል ተናግሮኛልና አልረሳውም። ሲዲው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይገባ ነው በፖስታ አሽጌ ለፓስተር ሚኪ ከደብዳቤ ጋር የላክሁለት። ከአምስት ዓመት በፊት በመሆኑ እርሱ ሊረሳው ይችላል። ጊዜውን፣ ሁኔታውን ሁሉ ጠቅሼ ጽፌለታለሁ።

 

ጥያቄ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦችን ከራስሽ ጋር አዛምደሽ ደስ በሚል መንገድ ታቀርቢያቸዋለሽ። ዮሐንስ 4 እና 11ን፣ እንዲሁም መዝሙር 91ን መጥቀስ ይቻላል። ሳምራዊቷን ሴት፣ “ከአንዱ ተጋብቼ፣ አንደኛውን ስፈታ” ከሚል አገላለጽ ጋር ታቀርቢያታለሽ። የሟቹ የአልዓዛርን እኅቶች ጌታን “አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን …” ያሉትን “እንዲህ ያለ ስንፍና ከአፌ አላወጣም” በሚል ታቀርቢዋለሽ። ስለዚህ ዐይነቱ አዘማመር ምን ትያለሽ?

አስቴር፡- የተፈለገውን ነገር ለማለት አንድ ምዕራፍ ላይ ጊዜን መውሰድ እና ታሪኩ ውስጥ ራስን መክተት አንድ ነገር ነው። የበሰለ ነገርን ለማውጣት ማለት ነው። ከዚያ አንጻር የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦችን ወስዶ፣ ዐውዳቸውን ተረድቶ ከዚያ ውስጥ የሆነን ነገር ማውጣት፣ የመልእክቱን ሙሉ ሐሳብ ማስተላለፍ ይቻላል። በሰዎች ሕይወትም ውስጥ ደግሞ እንደዚህ የሚቀመጥ ነገር ይኖራል። ገባህ አይደለ? መዝሙር ስንጽፍ እዚህ እዚያ፣ እዚህ እዚያ ሳንዘል ሙሉውን ሐሳብ በማቅረብ ሰዎች መልእክቱን እንዲረዱት ይረዳል ብዬ እላለሁ።

 

ፕሪቶሪያ ለአገልግሎት የሆነ ስፍራ ላይ ተጋበዝን። የሚያገለግለው ሰው ይሰብክ የነበረው ስለ ሳምራዊቷ ሴት ነው። “ኢየሱስ የሕይወት ውሃ ምንጭ ነው። የተጠጋው ሰው ደሞ የሕይወት ውሃ ከሆዱ ይፈልቃል።” እያለ ሲናገር ነበር። እኔ ግን ገረመኝ። ጌታ “ውሃ አጠጪኝ” ብሎ ምክንያት ነው የፈጠረው። ውሃ ሊጠጣ ሳይሆን፣ ሰበብ ፈልጎ በዚያ ስፍራ ቁጭ ብሎ ጠበቃት። አይገርምም? የእርሷ ሕይወት ግድ ብሎት ነው ይህን ያደረገው። ውሃ ስለ መጠጣቱ እዚያ ቦታ ላይ አልተጻፈም። ገባህ አይደለ?

 

ከዚያ ባሻገር ደሞ ስለዚህች ሴት ብዙ ጊዜ ይሰበካል። አምስት ባሎች እንደ ነበሯት፣ በአንዳቸውም እንዳልረካች፣ አሁን አብሯት ያለው ባሏ እንዳልሆነ ይነገርላታል። ግን ስለ እኛስ? ከስንት ነገር ጋር ነው ተጋብተንና ተቆራኝነት ያለነው? አሁን ያ ሰው ቆሞ እየሰበከ እያለ፣ እኔ ስለ ራሴ ነበር ሳስብ የነበረው። በሕይወት ጎዳና ላይ ብዙ ጓዝ ይኖራል። ትዳር አለ። ትዳር ውስጥ ስትገባ የጌታን ነገር በትዳር ምክንያት እርግፍ አድርጎ መተው አለ። ልጅ ይወለዳል። ከዚያ ደግሞ በልጅ ምክንያት ከልጅ ጋር ተቆራኝቶ፣ ከልጅ ጋር ተሳስሮ የጌታን ነገር መተውም አለ። ጌታን መተው አለ፤ እግዚአብሔር በውስጣችን ያስቀመጠውንም ነገር ደሞ እርግፍ አድርጎ መተውም አለ - በሥራ ምክንያት፣ በቢዝነስ ምክንያት፣ በባለጠግነት ምክንያት፣ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ምክንያት። እኔ እንዲያውም ሳስበው ይቺ ሴት አምስት ባሎች ነው ያሏት፤ እኔ ምን ያህል ባሎች እንደ ነበሩኝ ሳስብ ይገርመኛል። እውነቴን ነው የምልህ፤ ከእነዚያ ሁሉ አፋትቶኛል! አፋትቶኝ ስል ገባህ አይደለ? እና ከዚያ አንጻር ነው ይቺን ሴት ያየኋት።

 

የአልዓዛርን ደሞ ስትመለከት፣ “የምትወድደው ታሟል” ብለው ለጌታ መልእክተኛ ልከውበታል። መጥቶ እንዲፈውሰው። ግን አልመጣም። እያወቀ አልመጣም። ለምንድን ነው ያልመጣው? ብዙ ድውያንን ፈውሷል። ግን የሞተን ሰው በማስነሣት፣ በዚህ መንገድ የእግዚአብሔር የአባቱ ስም እንዲጠራ ፈለገና ኢየሱስ ዐውቆ ቆየ። ከዚያ አቅጣጫ ነው የታየኝ። “ፈጥነህ ብትመጣ፣ ብትገኝ በቤቴ … ጌታ ሆይ፤ ለምን ቀረህ? ለምን እንደዚህ …?” የሚያስብሉ ነገሮች ነበሩኝ። አንዳንድ ጊዜ መጨረሻ ላይ ስደርስ፣ እርሱ መጥቶልኝ ያለቀና ያከተመለትን ነገሬን ሲያስነሣው አይና “ለካ የስንፍና ቃል ነው ያኔ የተናገርኩት!” እላለሁ። ገባህ አይደለ? ያንን ዐይነት ንግግር ነው ልናገር የፈለግሁት። አሁን የሞቱና ያለቀላቸው የሚመስሉ ነገሮች፣ ብዙ ሬሳዎች በዙሪያዬ አሉ። መሞታቸውም ሆነ መሽተታቸው ግን የጌታን ክብር ሊያወጡ፣ የጌታን ስም ሊያስጠሩ፣ በእኔ ቤት የስሙን ሰንደቅ ሊያሰቅሉ ነው ብዬ እንድናገር፣ በጌታ ላይ ከትናንት ይልቅ እንድታመን ሆኛለሁ። ከዚያ አንጻር ነው እነዚህን ዝማሬዎች የዘመርኳቸው።

 

ሌላው ደግሞ መዝሙር 91 ነው። ሰው በዘመኑ ብዙ ነገርን ትምክህት ያደርጋል። ብዙ ነገሩን። እኔ ግን እኔ ጋ ስትመጣ ግን፣ በቃ በእግዚአብሔር ሥር ከመኖር ይልቅ ምን ትምክህት አለኝ? የእግዚአብሔር ከመባል ውጭ፣ በአደባባይ የምመካበት፣ በሰዎች ፊት የምመካበት ምናለኝ? እኔን ከእግዚአብሔር ነጥዬ ላውራ ብል ከድካሜ ውጭ የማወራው ምንም ነገር የለኝም። ምንም! በአገልግሎት ራሱ፣ አሁን ዝማሬው እዚህ ከደረሰ በኋላ፣ ሰዎች በተለያየ አረዳድ፣ “ምን ዐይነት ሴት ናት?” በማለት ብዙ ነገሮችን ሊናገሩ ይችላሉ። እኔ ግን ስለ ራሴ የማውቀው ድካሜን ነው። ደጋግሜ መውደቄን ዐውቃለሁ። ደጋግሜ በሕይወት ውጣውረድ ውስጥ፣ እግዚአብሔርን ባለመፈለግ ውስጥ ያለፍኩባቸው መንገዶች አሉ። የጌታን ነገር በመርሳት፣ በመተው፣ በድካም፣ በተለያዩ ነገሮች ውስጥ ዐልፌአለሁ። ግን የእርሱን ብርታትም ደሞ አይቻለሁ። በእርሱ ስጀግን አይቻለሁ። በቃ! እንደገና መነሣት ሲሆንልኝ አይቻለሁ። አሁንም ትምክህቴ ጌታ ነው። የምጓደድበት፣ የምመካበት፣ ነገን እንድኖር ደግሞ የሚያስናፍቀኝ የእርሱ ከእኔ ጋር መሆን ነው!

 

ጥያቄ፡- “መንፈስ ቅዱስ” በሚለው ዝማሬሽ ላይ፣ “አንድ የሆነ ጉዳይ ከኔ ጋር እስክትጨርስ ድረስ፣ አይደለም ለጊዜው ወደ አብ እስከምትመለስ” ያልሽው ምን ለማለት ነው? ወደ አብ የተለመለሰው ጌታ ኢየሱስ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም እኮ!

አስቴር፡- ኢየሱስ ነው ወደ አብ የተመለሰው፤ እውነት ነው። ከመሄዱ በፊትም፣ “አጽናኙን እልክላችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላል” ብሎ ነበር። ያ ማለት፣ ከዚያ በፊት መንፈስ ቅዱስ ምድር ላይ አልነበረም ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ለሆነ ሥራ እየመጣ፣ የሆነ ሥራ ሠርቶ የሚመለስ ነው የሚመስለኝ። ልክ ላልሆን እችላለሁ። በሚቀጥለው ዝማሬ ላይ ላስተካከል እችላለሁ። አሁን ግን አዲስ ኪዳን፣ ኢየሱስ ካረገ በኋላ ሁሌ በውስጣችን የሚሆን፣ አብሮን የሚሆን መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል። “ሁሌ ከእኔ ጋር ነህ፤ አትሄድብኝም” ለማለት ነው።

 

ጥያቄ፡- “ወደ አብ እስከምትመለስ” ማለትን ግን ምን አመጣው? አባባሉ ስሕተት ነው።

አስቴር፡- ተቀብያለሁ።

 

ጥያቄ፡- እያንዳንዱ አድማጭ የየራሱ ምርጫ ቢኖረውም፣ ከመዝሙሮችሽ መካከል “አዛኝ ባትሆን፣ አምላኬ ባትሆን፣ ... ፈቅደህ ባትምረኝ፣ መክረህ ባትመልሰኝ፣ ምን ይሆን ነበር ዕጣዬ?” የሚለው ለብዙዎች ልብ ቅርብ ይመስለኛል። እዚህ ጋ ምስኪን ሰው ይታየኛል። እንዴት እና በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ዘመርሽው?

አስቴር፡- ይሄ ሁሉ የእኔን ድካም፣ የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት፣ የእርሱን ደጋፊነት፣ የእርሱን ተሸካሚነት ነው የሚያሳየው። ሰው ደግሞ በምድር ላይ እስከ ኖረ ድረስ በተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ ያልፋል። በፈቃዱ ይደክማል፤ በነገሮችም ተጎትቶ ሊሆን ይችላል። ሰው ከጌታ ቤት ሸሽቶ ሄዶ እንኳን፣ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ፣ የሚጠብቅ ማንነት፣ የሚሸከም ማንነት አምላካችን አለው። ትክክለኛውን ጊዜ ባላስታውስም ይሄ ፍቅሩ፣ የፍቅሩ ጥልቀት በገባኝ ጊዜ በዚህ ዝማሬ ብዙ እንዳለቀስኩኝ አስታውሳለሁ። ደጋግሜ ከዘመርኳቸው ዝማሬዎቼ አንዱ ይሄኛው ነው። ብዙ ቦታ ላይ ዘምሬዋለሁ። ሕይወቴ ነው። የእኔ ዝማሬ ነው። አንተን ሳያስለቅስህ፣ አንተን ሳይገባህ፣ አንተን ሳያረካህ ወደ ውጭ የምታወጣው ነገር የሰዎችንም ሕይወት ይነካል ማለት አስቸጋሪ ነው። መጀመሪያ እኛ ጋር መብሰል፣ የእኛን ነገር መንካት አለበት። የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዴ የሚፈልቀው እኮ መጀመሪያ እኔን አርክቶኝ ነው። እኔ ገብቶኝ ነው። እኔ ያለፍኩበትን ነገር ለሰዎች ስናገር ነው። ካልሆነማ የገደል ማሚቶ ነው የሚሆነው፤ ሰዎች ጋ ተጽእኖ የማይፈጥር። ሕይወቴ ስለሆነ ይመስለኛል ሰዎች እኔ የሆንኩትን ነገር እንደገና መልሰው ሊያንጸባርቁ የቻሉት ብዬ አስባለሁ።

 

ጥያቄ፡- እግዚአብሔርን በአምላክነቱ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ እጅግ መልካም መዝሙሮች አሉሽ። ለምሳሌ “ትልቅ የሆነውን”፣ “እስኪ ይንገረኝ”፣ “ክብር የበቃህ ነህ” የሚሉትን መጥቀስ እችላለሁ። ስለዚህ ዐይነቱ አዘማመር የምትዪው አለሽ?

አስቴር፡- ይሄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው እላለሁ። እኔም ራሱ ያልደረስኩበት። ያልደረስኩበት ብዬ ስልህ፣ በምድር ስንኖር በተለያዩ ዐይነት የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ እናልፋለን። አንዱ የሚያሳርፍ መስሎን፣ አንዱ ውስጥ እንገባለን። ብቸኝነት ያሠቃየው ትዳር ውስጥ ይገባል። ትዳር ውስጥ ደግሞ ሲገባ ልጅ ይወልዳል። እያንዳንዱ ነገር ግን የራሱ የሆነ ችግር አለው። ሕይወት ሙሉ እንግዲህ ፈተና ነው። ከእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች በላይ እግዚአብሔርን ማክበር ግን እንዴት መታደል ነው! ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት ማውራት መታደል ነው።

 

ዕንባቆም እንደ ሆነው ማለት ነው። ዕንባቆም የክስ ፋይሎችን ይዞ ነው ወደ እግዚአብሔር የገባው። ሰዎችንም ሊከስስ ነው የገባው። ግን ከገባ በኋላ የተናገራቸው ነገሮች አሉ። “እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል” ያለው። እና ያ ማለት ምንድን ነው? ሰው በተግዳሮቶችም ሆነ በምንም ዐይነት ነገር ውስጥ ቢያልፍ፣ ከከበበው ነገር ይልቅ እግዚአብሔርን ማየት ከቻለ፣ ያ ሰው የታደለ ነው። ሩጫዬም ወደዚያ ነው። አሁን ምን ይናፍቅሻል? ብትለኝ፣ በዙሪያዬ ስለ ከበቡኝ ነገሮች ሳይሆን፣ ከነገሮች በላይ የሆነውን እርሱን ማድነቅ! የምድሩን መርሳት! ከምድር፣ ከሚጎትት ከማንኛው ነገር፣ የእግዚአብሔርን ታላቅነት አሳንሼ እንዳይ በዙሪያዬ ሆኖ ከሚጎተጉተኝ ከማንኛውም ነገር ራሴንን አላቅቄ እርሱን ብቻ እያየው መዘመር! በእርግጥ እግዚአብሔርን የማወቅ ቁመታችን በጨመረ መጠን ይመስለኛል ወደዚህ ዐይነት ነገር የምናልፈው። እና ያ ምኞቴ ነው።

 

ጥያቄ፡- አልበምሽን የሰጠሺው ለቤተ ክርስቲያን ነው - ለገርጂ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን። ቤተ ክርስቲያነቱ በቅርቡ የተመሠረተች ትመስለኛለች። እንዴት መረጥሻት?

አስቴር፡- እኔ ከአገር ከወጣሁ ዐሥር ዓመቴ ነው። ያደግሁት በወንድማማች ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ነው። አገር ቤት ካሉ ቤተ ክርስቲያኖች ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት የለኝም። አያውቁኝም። ስለዚህችኛዋ ቤተ ክርስቲያን ዕድሜም አላውቅም። የአማኑኤል አጥቢያ መሆኗን ብቻ ዐውቃለሁ። ፓ/ር ዘርዬ እዚህ አገር ለአገልግሎት ሲመጣ ሦስት ጊዜ ያህል በአገልግሎት ተገናኝተናል። ሲዲ ለመሥራት ሐሳብ እንዳለኝም ሳያውቅ፣ ገርጂ ምን ዐይነት ሰፈር እንደሆነ፣ ሕፃናት በምን ዐይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ በአካባቢው ስለሚካሄዱ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ያጫውተኝ ነበር። ቤተ ክርስቲያናቸው ምን ዐይነት እንቅስቃሴ ላይ እንዳለችና በሕፃናቱ ላይም ስለምታደርጋቸው መልካም ነገሮች ፎቶዎችን ጭምር ያሳየኝ ነበር። ወንጌልን እየሠሩ እንደሆነ ስለ ነገረኝ ዐውቃለሁ።

 

ከዚህ ሁሉ በኋላ ሲዲውን ሠራሁ። ገቢው ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናትና ለባልቴቶች እንዲሆን ነበር የማስበው። ማነው ይህን የሚሰጥልኝ? እንዴትስ ነው የሚደረገው? የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ነገሩ ልቤ ላይ ከበደብኝና ጾም ጸሎት ይዤ በጌታ ፊት ሆንኩ። ልክ በሁለተኛው ቀን ላይ፣ በተንበረከክሁበት ነው ስልክ የተደወለው። ፓ/ር ዘርዬ፣ “ለምን ለቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ነገር አትሰጪም? እንዲህ እንዲህ ዐይነት ነገር አለ” ብሎ ሲለኝ፣ ያው አስቀድሞም አውርተነው ስለ ነበር አልከበደኝም። ልጸልይበት አልኩት። አሰብኩበት። ውስጤ ሰላም ስለነበረ ተስማማሁ። አንዳንድ ሰዎች ከአገር ቤት ለአገልግሎት ወደዚህ ሲመጡ፣ “ጥሩ መሬት ላይ ነው የዘራሽው” ብለውኛል።

 

በአውሮፓና በአሜሪካ ያለው ግን ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ አይደለም። ማሰራጨቱንም ምኑንም ምኑንም እኔ አይደለሁም የምሠራው። ከሥራ ጋር፣ ከቤተሰብ ጋር ስለማይመቸኝ ግሩሜ ነው እየተባበረኝ ያለው። ይህኛውን ደግሞ፣ መጀመሪያ አስቤ ለነበረው ለሕፃናት፣ ለባልቴቶች፣ ለዐቅመ ደካሞች እንዲውል እግዚአብሔር ይረዳኛል። ለዚያ ዓላማ አውለዋለሁ።

 

ጥያቄ፡- በመንፈሳዊ ሕይወትሽ ወይም በዝማሬሽ የማን ተጽዕኖ ያለብሽ ይመስልሻል? ማንኛችንም ብንሆን ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ አንሆንም፤ ግና የማን ጉልህ ተጽዕኖ አለብሽ?

አስቴር፡- እንግዲህ ከልጅነቴ ጀምሮ ዝማሬዎችን እሰማለሁ። በጣም ልጅ ሆኜ እነ ታምራት ኀይሌን፣ እነ ተስፋዬ ጋቢሶን እነ ደረጄን ስሰማ አስታውሳለሁ፤ ከበፊቶቹ። ከዚያም እነ ፀሓይ ዘለቀን። በእያንዳንዱ የዕድሜ ደረጃ የወጡትን ዘማሪዎች መዝሙር እወዳለሁ፤ እሰማለሁ፤ እዘምራለሁ። ልጅ ሆኜ ነው መዘመር የጀመርኩት፤ ገና ታዳጊ በምባልበት ጊዜ። መድረክ እየተሰጠኝ መዘመር በጀመርኩበት ጊዜ ግን ከሰው የተሰጠኝ የመጀመሪያ ስጦታ የአዜብ ኀይሉ ካሴት ነው። በስጦታነት ያገኘሁት ስለሆነ ነው መሰለኝ በጣም እሰማው እንደ ነበር በደንብ ነው የማስታውሰው። ዝማሬዎቿን ከመስማት ብዛት ድምፅዋን አመሳስዬ እስከ መዘመር ሁሉ ደርሻለሁኝ።

 

ጥያቄ፡- “እምቢ” የሚለውን?

አስቴር፡- “እምቢ”ን ሳይሆን፣ “ጽድቅን እንዲያወራ ምላሴ” የሚለውን መዝሙር በጣም ነበር የምዘምረው። አሁን ከሚደርሱኝ መልእክቶች መካከል፣ “የአዜብ ግርፍ ነሽ” የሚሉ አሉበት። ለነገሩማ ሊሊንም የሚጠቅሱልኝ አሉ። አዜብ ግን ይበልጥ ተጽዕኖ አሳድራብኛለች። እንዴት እንደ ሆነ አላውቅም፣ ግን አንድ ቀን ትዝ ይለኛል፤ እኔ ረጅም መንገድ ለአገልግሎት እየሄድኩኝ፣ እሷም ከባለቤቷ ጋር ከፊት ለፊት እየሄደች እየተከተልኳት የገባችበት ታክሲ ውስጥ ሁሉ ገብቻለሁ። “ምናለ ባለቤቷ ከዚያ ዞር ቢልና ተጠግቻት ከጎኗ ሆኜ ባወራኋት?” ሁሉ ብያለሁ።

 

ጥያቄ፡- ይሄኔ እኮ አንቺንም እንዲህ የሚልሽ ይኖራል።

አስቴር፡- ሊኖር ይችላል። ዞሬ አላየሁም እስካሁን። የሚገርምህ አዜብ እዚህ ያለሁበት አገር ብትመጣም፣ በሥራ ምክንያት መሄድ አልቻልኩኝም። የተጋበዘችበት የአገልግሎት ቦታ ማለት ነው። እንደምወዳት ልንገራት ብዬ በመጨረሻው ቀን ሄድኩኝ። መቆም አቃተኝና እግሮቼ ተብረከረኩ። ለሁሉም ዘማሪዎች ነው አክብሮት ያለኝ። ግን በሕይወቴ ላይ እንደዚህ ተጽዕኖ ለፈጠሩብኝ ሰዎች ደሞ ይበልጥ አክብሮት አለኝ። ልክ አገልግላ እንደ ጨረሰች፣ ቆሜ እያወራኋት ለካ እንባዬ መውረድ ጀምሯል። “እኔ በጣም ነው የምወድሽ” አልኳት። አገር ቤት እርሷን ተከትዬ የሆንኩትን ሁሉ አጫወትኳት። የገባችበት ጸጉር ቤት መሄዴን ሁሉ ነገርኳት። “እና ለምን አላናገርሽኝም?” አለችኝ። መንቀጥቀጥ ጀመርኩ። ቻው ካልኳት በኋላ፣ “ምን ሆኜ ነው?” ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ። I love her so much! ውድድ ነው የማደርጋት። በጣም። በስማም!

 

ጥያቄ፡- የምትወጂው ምግብ ምንድን ነው? ምናልባት አድናቂዎችሽ ከጋበዙሽ ብዬ ነው!

አስቴር፡- የቤት ከሆነ ቀይ ሽሮ። ምንም ምንም ተከታይ የሌለው ማለት ነው።

 

ጥያቄ፡- በዳቦ?

አስቴር፡- አንተ ደሞ? በእንጀራ ነው እንጂ! በጥቁር እንጀራ። ከቤት ይህን ምግብ ስመርጥ፣ ከውጭ ከሆነ ግን ቀምሼ የጣፈጠኝን ሁሉ መብላት እችላለሁ።

 

ጥያቄ፡- እንደ እኔ፣ ሰው የከፈለበት ምግብ ሁሉ፣ የተጋበዝሽው ምግብ ሁሉ አይጣፍጥሽም?

አስቴር፡- ሰው የጋበዘኝን ሁሉ አልበላም፤ የጣፈጠኝን እበላለሁ።

 

ጥያቄ፡- ምግብ ላይ ባለሞያ ነሽ?

አስቴር፡- ትምህርት ቤት ገብቼ የምግብ ዝግጅት አልተማርኩም። ስለዚህ የምግብ ባለሞያ አይደለሁም።

 

ጥያቄ፡- ባለሞያ ማለትን “ፕሮፌሽናል” አድርገሽ ወሰድሽው ማለት ነው?

አስቴር፡- አዎን!

 

ጥያቄ፡- እሺ፤ ባልሽ ምን ይልሻል?

አስቴር፡- ለባሌ ባለሞያ ነኝ። እኔ ቤት ካበሰልኩ ውጭ አይበላም ማለት ነው።

 

ጥያቄ፡- እርሱማ ምን ምርጫ አለው?

አስቴር፡- (ሣቅ)

 

ጥያቄ፡- በዚህ ሥራ እነማንን ማመስገን ትፈልጊያለሽ?

አስቴር፡- የጌታን አውርቼ አልጨርስም። ከእርሱ በታች እግዚአብሔር ስለ ሰጠኝ ሰዎች ላውራ። እናቴን በጣም ነው ማመስገን የምፈልገው። ዝማሬን ስጀምር ግጥሞቹን ታይልኝ ነበር። በጣም ትጸልይልኛለች፤ እስካሁን ድረስ ማለት ነው። አንዳንዴ በስንፍናዬ ላበላሽ ያልኳቸውን ነገሮች በሙሉ፣ ማንነቴን እየነገረችኝ፣ በእኔ ውስጥ እግዚአብሔር ሊያደርግ ያለው ትልቅ ነገር መኖሩን እየነገረችኝ ብዙ ነገሮችን አስተካክላልኛለች። እናቴ ዘማሪ ናት። እርሷ ማድረግ ያልቻለቻቸው ነገሮች በእኔ እንዳይደገሙ በጣም በብዙ ምክር ደግፋኛለች። እና በጣም እወዳታለሁ። ጌታ ኢየሱስ ብርክ ያድርጋት።

 

ቀጥሎ ደግሞ እግዚአብሔር የሰጠኝን ባለቤቴን በጣም ነው የማመሰግነው። ብዙ ረድቶኛል። ቤት ውስጥ ሴት ማድረግ የሚገባትን ነገር ሁሉ እያደረገ ነው የሚደግፈኝ። ሦስት ልጆችን ማሳደግ በጣም ይከብዳል። እነዚያን ነገሮች በሙሉ እያደረገ፣ እኔ ውስጥ ያለው ነገር እንዲወጣ በጣም አግዞኛል። በጣም ረድቶኛል።

 

ሌላ ደግሞ ዳዊት ጌታቸውን! ሙዚቃውን ለመሥራት እሺ ስላለኝ በጣም ነው የማመሰግነው። መዝሙሮችንም አብሮኝ መርጧል። ከምን አንጻር እንደምልህ ልንገርህ? ዳዊት ከሳዖል ሸሽቶ ወደ አዶላ ዋሻ በሄደ ጊዜ፣ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተዋል። የተጨቆኑ፣ ዕዳ ያለባቸው፣ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው ነበር። እናም እነዚያን ሰዎች ተቀብሎና አሠልጥኖ ከእርሱ ጋር ከወጡ በኋላ የተጻፈላቸው ነገር አለ። “የዳዊት ኀያላን” ነው የተባሉት። እንግዲህ እኔም ተስፋ በቆረጥኩበት ሰዓት ላይ፣ “ቢቀርስ!” ባልኩበት ጊዜ ነው ዴቭን ያገኘሁት። እና እግዚአብሔር ይባርከው፤ ከመጠቀሚያ መንገዶች አንዱ ስላደረገው።

 

የደቡብ አፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ፓስተሮችንም በሙሉ አመሰግናለሁ፤ መድረካቸውን ስለ ከፈቱልኝ። እኔ እዚያ የምዘራው ነገር የሕዝባቸው የማደግ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ሌላም ነገር ሊሆን ይችላል። እናም ከዚያ አንጻር አምነው መድረካቸውን ስለ ሰጡኝ በጣም ነው የማመሰግናቸው። በገንዘብ የረዱኝ አሉ፤ ነቢይ ጌች እና ነቢይ ኢዩ። ፓስተር መስፍን የሚባል የአማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ፓስተርንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ዴቭ የመጣው በቤተ ክርስቲያኒቱ ኮንፈረንስ ላይ ለማገልገል ቢሆንም፣ “መጠቀም ትችያለሽ” በማለት ዴቭ ከእኔ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ ፈቅዶልኛል። የሁሉም አሻራ እላዬ ላይ አለ። የገርጂ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ፓስተር የሆነው ዘርዬ ደግሞ አገር ቤት ያሉ ነገሮችን ሁሉ በማስጨረስ በብዙ ረድቶኛልና ምስጋናዬ ይድረሰው። በመጨረሻም፣ የማገለግልባትን ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናን እና ዘማርያን (“ሀ” እና “ለ” የመዘምራን ቡድንን) እጅግ አመሰግናለሁ!

Read 20180 times Last modified on Monday, 26 June 2017 10:36
Paulos Fekadu

ጳውሎስ ፈቃዱ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፣ በሞያው መምህር ነው። በነገረ መለኮት እና በኮምፒውተር ሳይንስ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዎች ያሉት ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርን በአእምሮውም ለመውደድ የሚሻ አማኝ ተደርጎ ቢወሰድ ይመርጣል።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 13 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.