You are here: HomeYouth Cornerኢንተርኔትና ሚዲያ ለዘመኑ ወጣት እድል ወይስ ፈተና ?

ኢንተርኔትና ሚዲያ ለዘመኑ ወጣት እድል ወይስ ፈተና ?

Written by  Wednesday, 25 March 2015 00:00

ዘመን ዘመንን እየወለደ ሲሄድ ክስተቶች ፣ በጊዜ ሂደት ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሁም የግንኙነት ዘዴዎች ሕይወትን ከማቀላጠፍ አንፃር የሚጫወቱት ድርሻ ቀላል እንዳልሆነ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ በተለይ በኢንፎርሜሽን ግንኙነት ቴክኖሎጂ ረገድ .የኮምፒውተር ኢንተርኔት ግንኙነት፤ የሞባይል ስልክ ግንኙነት፤ የሳተላይት ቴሌቪዥኖች እና ሌሎችም እጅግ የረቀቁና አለምን በፍጥነት ወደ እንድ መንደር እያገናኙ ያሉ የግንኙነት መንገዶች ናቸው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት አለም ያለችበትን የእድገት ደረጃ “አለም በጣቶችህ ጫፍ ነች (The world at your finger)” እስከመባል የደረሰው የቴክኖሎጂ ሽግግር ያመላክታል፡፡ የፈለጉትን መረጃ በፈለጉት ሰዓት፣ በኮምፒውተር ኪቦርድ፣ በሞባይል በተን፣ በቴሌቪዥን ሪሞት አለምን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ዘመኑ የደረሰበት የአይሲቲ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች እለት እለት በሚያደርጉት ግንኙነት ውስብስብና ዙሪያ ጥምጥም ይኬድባቸው የነበሩ ኋላቀር እና የተንዛዙ አሰራሮችን ከማቅለልና እና ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር ያበረከተው አስተዋፆ እድሜ ለቴክኖሎጂ የሚያሰኝ ነው ፡፡

 

ሚዲያና ኢንተርኔት የሰው ልጅ መረጃን ለማግኘት የሚያደርገው ሩጫ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ዛሬ ብዙ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን፣ የት/ቤት ጓደኞቻቸውን በኢንተርኔት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ማግኘት እየተለመደ የመጣ ሆኗል፡፡እንዲሁም ብዙ ክርስትያኖች ቤታቸው ተቀምጠው በተለያዩ ቻናሎች የእግዚያብሄርን ቃል መማር እንዲሁም በተለያዩ አለማት ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር አንድ ላይ ለማምለክ መቻላቸው ከቴክኖሎጂ የተገኘ ቱሩፋት በመሆኑ በዚህም ረገድ እግዚያብሄርን ልናመሰግን ይገባል ፡፡

 

እነዚህ የግንኙነት ዘዴዎች ከሚቀርብልን የመልዕክት ልውውጥ በላቀ ሁኔታ አሁን አሁን በካሜራ በመታገዝ E-vidio ከምንፈልገው ሰው ጋር እተያየን መረጃ መቀበል መቻል የመረጃ አቅርቦትን የበለጠ ተወዳጅ እና ቀላል ከማድረጉም በላይ ምን ያህል የሰው ልጅ ህይወት ውስጥ አይነተኛና አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን እንረዳለን ፡፡

 

በዚህም በእኛ ትውልድ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የሰው ልጅ ከኮምፒውተር ጋር ያለው ቁርኝት እና ጥብቅ ጓደኝነት እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ face bookን ብንመለከት በአለም ዙሪያ ከ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከመረጃ መረብ ውስጥ ያሉ የአንድ መንደር ነዋሪዎች ናቸው ብለን ብናስብ በአገር ደረጃ ከቻይና ጋር በመስተካከል የአለም ሁለተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ሃገር facebook ትሆን ነበር፡፡ በዚህ በ facebook የሚደርገው የመረጃ ልውውጥ ከመቼውም ጊዜና ከሌሎች ግንኙነቶች በላቀ መልኩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 150 ቢሊዮን መልዕክቶች በፌስቡክ እንደሚቀያየሩ መረጃዎች ያሳይሉ ፡፡ይህ ማለት ደግሞ የአለም ህዝቦች ማህበራዊ ግንኑነታቸው ተፈጥሮአዊ መሆኑ እየቀረ ወደ ቴክኖሌጂው የመረብ ግንኙነት ምን ያህል እየተቀየረ እንደሆነ የሚያሳይ ፍንጭ ነው፡፡

 

የFacebook ፈጣሪና ባለቤት የሆነው የ29 አመቱ አይሁዳዊ ማርክ ዙክበርግ እንደሚገልፀው face bookን ሰዎች ከምንግዜውም የበለጠ ስሜታቸውን ሃሳባቸውን የሚገልፁበት የግንኙነት ማጠናከሪያ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል እየሰራ መሆኑን በtime መፅሄት ላይ በሰጠው አስተያየት ላይ ግልፆታል፡፡ የአለም ህዝቦች ከምንግዜውም በበለጠ ሁኔታ ማህበራዊ ድህረ ገፆችን ለረጅም ሰዓት እየተጠቀሙ ያሉበት ጊዜ መሆኑን እንዲሁም የማህበራዊ ድህረ ገፆች face bookን ጨምሮ ማህበራዊ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እያሳረፉ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች እያስታወቁ ይገኛሉ፡፡ ተፈጥሮአዊ ከሆነው ሰው ልጅ የማህበራዊ ግንኙነት ወይም social DNA ይልቅ በግለኝነት ላይ እየተመሰረተ መምጣቱ ሌላኛው ስጋት ነው፡፡

 

አንዳንድ ጊዜም ሚዲያ ለመልካም እድገት መሰረት እንዲያመጣ የተሰራ ቴክኖሎጂ ቢሆንም በውስጡ የያዛቸው የክፋት አሰራሮች ትውልዱን አንቆ በመያዝና የክፋት መረብ በመሆን የጨለማውን አለም እንደሚያገለግል ማወቅ ይጠበቅብናል ፡፡ ለምሳሌ Google የተባለው ድህረ ገፅ ባለፈው ዓመት የለቀቀውን መረጃ ብንመለከት በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መረጃ የመፈለግ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልፆ እንዲሁም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መረጃዎችን የሚያቀብሉ ድርጅቶች የዛን ያህል መጨመራቸው የቴክኖሎጂው ሽግግር እድገት ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ በGoogle ሳይት ብቻ በመጠቀም እስከ አሁን 3 ሚሊዮን pornography video ጣቢያዎች እንዲሁም በየቀኑ ከ1000 ያላነሱ ሣይቶች እንደሚጨመሩ የዘገበ ሲሆን እነዚህንም ጣቢያዎች አዘውትረው በደምበኝነት የሚጠቀሙት እድሚያቸው ከ12-17 የሚደርሱ ወጣቶች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት ምን ያህል በትውልዱ ላይ የተጋረጠ መሆኑንና ስር እየሰደደ መምጣቱን ከመረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ በላይ የጠቀስናቸው የpornography ሳይቶች በአለም ዙሪያ ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሏቸውና አመታዊ ገቢያቸውም 56 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የደረሰ ሲሆን ድርጅቶቹ ከዚህ በተሻለ መልኩ አገልግሎታቸውን በስፋት መስጠትና ግንኙነት ባሉበት በድምፅና በምስል እየተያያዘ እንዲሆን ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡ ይህም ተተኪ ትውልድ ላይ ጠላት ምን ያህል መጥፎ ዘር እየዘራ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡

 

በአገራችን ያለውን የኢንተርኔት አጠቃቀም ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ጥናቶችን በበቂና በተደራጀ መልኩ ለማግኘት ባይቻልም አብዛኛው ወጣት የኢንተርኔት እና ሚዲያ ተጠቃሚ እንደመሆኑ ዞሮዞሮ የዚህ ችግር ሰለባ መሆኑን በዳሰሳ ጥናታችን ታዝበናል፡፡ በትውልዱ ላይ የተጋረጡ መረጃዎችን የመፈለግና በመረጃ ውስጥ ያሉትን መልዕክቶች እንደወረደ መቀበል፤ በኢንተርኔት የሚደረግ ትውውቅ፣ ጓደኝነት፣ ብሎም ማንነትን ሳያሳውቁ ለጋብቻ መተጫጨት፣ እድልን ለማወቅ የሚደረግ የጥንቆላ አሰራር ወይም horoscope እንዲሁም የተለያዩ ድህረ ገፆች ላይ እና በዩ ቲዩብ የሚለቀቁ የሃሰት ትምህርቶች ዋነኞቹ የችግሩ ምንጮች ሲሆኑ የእነዚህም ውጤት የባህል ውድቀትን፣ የአስተሳሰብ ዝቅጠትን እንዲሁም የመንፈሳዊ ህይወት ድንዛዜን እንደሚያስከትሉ በቀላሉ በምዕራባዊያን ከአሜሪካውያን ህይወት ኪሳራ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደኛ ሃገር ያሉ ታዳጊ ሃገሮች ከድህነት ለማውጣት የሚደረጉ መፍገምገም በአብዛኛው የመንግስት ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ይልቅ ማህበራዊ ድህረ ገፃች ላይ በመጠመድ የሚያጠፉት ጊዜ በሃገር ኢኮኖሚ ስራ ከመበደል አንፃር የሚያመጣው ኪሳራ ምን ያህል እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም ፡፡

ዛሬ ዛሬ ትልልቅና ጠንካራ የነበሩ ቤት ለቤት ህብረቶች፤ የፀሎት ቡድኖች፤የቤተሰብ ፕሮግራም ፤ የዩንቨርሲቲ እና ኮሌጅ ህብረቶች በአውሮፓ፣ በአሜሪካ የሚለቀቀው ተከታታይና ሳምንታዊ ፊልሞች ፤የሃሰት ትምህርቶች፤ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን መቋቋም አቅቷቸው በማዕበሉ እተናወጡ እንዳሉ በየቤታችን የምንመለከተው ችግር መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ለበረከት የተሰጠን ስጦታ እርሱ ራሱ ተመልሶ የበረከታችን ጠላት ከሆነ በረከት ትርጉሙ ምንድነው? እግዚአብሄርን ልናከብርበት የተሰጠን ስጦታ መረጃን ለማግኘት ሁኔታዎችን እንዲያሰፋ የገዛነው ቴሌቪዥን እንዲሁም ለግንኑነታችን አድማስ እንዲሰፋ የያዝነው ኮምፒውተር በውስጡ ግን እኛን የሚያጠምድ የክፋት ወጥመድ እንዲሆን ከተባበርነው እኛን ከህይወት እንዲያርቀን ከፈቀድንለት ከበረከት ይልቅ የክፋት መሳሪያ ከሆነ ነገሩን ለማግኘት የፈለግንበትን ልብ ልንፈትሸው ይገባል ፡፡ ይልቁንም እኛ ብርሃን ልንሆን የተጠራን የእግዚአብሔር ልጆች በጨለማ ውስጥ ለሚፍገመገመው ትውልድ፣ በክፋት ወጥመድ የተያዘውን ወጣት ለመታደግ እንደ ዜጋ ብሎም እንደ እግዚአብሄር ልጆች ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅብናል ጉዳቱ የሁላችንንም የልብ ጓዳ የሚነካ፣ ቤተሰብን የሚያፈርስ፣ ስብእናን የሚያረክስ፣ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል፣ እንደመሆኑ ዝም ብለን ልንመለከተው አይገባም:: መፅሐፍ ሲናገር "መንፈሱን የማይጠብቅ ሰው ቅጥሩ እንደፈረሰ ከተማ ነው" (ምሳሌ 11፤4) እንደሚል ወደ አእምሯችን የሚገባው እና የምንመለከተውን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ የሰው ልጅ መረጃን የማግኘት መብቱ መገደብ እንደሌለበት የሚታወቅ ቢሆንም መረጃንም እየመረጡ መጠቀም ብልህነት ነውና የምንሰማውን መምረጥና መመርመር ይኖርብናል፡፡

 

Read 9172 times
Pastor Fitsum N.Demisse

Youth Pastor @ Bible Army International Church

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 26 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.