You are here: HomeYouth Cornerአውስቦት

አውስቦት

Written by  Thursday, 05 February 2015 00:00
ናሁሠናይ አፈወርቅ ናሁሠናይ አፈወርቅ

“ከአካል ጽዋ የነፍስን ወይን ሲጎነጩ፣ ያን ጊዜ ፍቅር ተባርኳል፡፡”  ሪቻርድ ጋርነት

 

አውስቦት ለዘር፣ ለውኀዳዊ-አንድነትና ለአካላዊ እርካታ በእግዚአብሔር የተነደፈ ነው፡፡ በጥልቀት የታሰበበትና በርቀት የታለመበት የተፈጥሮ ገጽታ ነው፡፡ ንድፉ ላይ ያለው አኀዝ “ሁለት” ሲሆን ዓይነቱ ደግሞ ሁለቱን ተቃራኒ (ተቀራራቢ) ፆታን ያማክላል፤ “ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው…ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ 1፣27)፡፡ የመጀመሪያውም የጋራ ትእዛዝ “ብዙ ተባዙ” (ቁ.28) ሆነ፡፡ ሥነ ሕይወታዊና ሥነ ልቦናዊ ውኀደት፤ በፈቃድ (በይሁንታ) ወደ አንድነት፣ በአንድነት ደግሞ መብዛት፡፡

 

የትእዛዛዊው ባርኮት ፍጻሜ የሚያገኘው በአውስቦት ነው፤ ከሰው ተፈጥሮ ጋር ከመጀመሪያውም ተቀምሞ በተቀመጠ፡፡ ይህም የተቀበልነው ሳይሆን የሆንነው ወይም ሆነን የተገኘንበት ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ማንም አውስቦትን ለአቅመ አዳም ወይም ሔዋን ሲደርስ የተላበሰው አይደለም፤ በውስጡ ቆይቶ በተፈጥሮ ሂደት እየጎለበተ የሚሄድ እንጂ፡፡ እንደየ እድገት ደረጃውም በሰውነታችን እየታወቀን የሚሄድ፡፡

 

ጅማሬ ያለው ነገር ፍጻሜ እንዳለው ሁሉ ይሄም ስሜት በእድገት አልፎ የሚከስም ነው፡፡ ሕፃን የአውስቦት ማንነት ኖሮት ያ እንደማይሰማው ወይም እንደማያጓጓው ሁሉ በዕድሜ የገፋም ሰው እንደዚያው እየሆነ ነው የሚሄደው፤ የመጽሐፍ ቅዱሶቹ አብርሃምና ሣራ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ፤ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል” (ዘፍ 18፣12) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ሣራ ልጅ ከመበጀቱ ወይም ከመጸነሱ በፊት ሩካቤ ጅማሬው እንደሆነ ነው ያጸናችው፤ ቆመን (ኖረን) በሕይወት ሂደቱን ሳናጤን የሚጀምረው ስሜት፣ ያው እንደ ቆምን እንዲሁ ሳይታወቀን እየደከመ ይሄዳል፡፡

 

እንግዲህ ሰው ከአውስቦት ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ይሄ በዔደን ገነት ስንሠራ አብሮን የተበጀው ነገር ፍጥረትን ሲቀድም፣ ሲያሰናክልና ከአምላኩ ጋር ሲያጣላ ኖሯል፡፡ የአያያዝ ጉድለቱ ግን እንደ ርኩስ ነገር የሚያስቆጥረው አይሆንም፡፡ የትኛውንም ስሜታችንን ሠርተን እንዳላመጣን ሁሉ አውስቦትም የተላበስነው ክስተትና ስሜት እንጂ ያመነጨነውና እኛው ያሳደግነው አይደለም፡፡ ሰው ይሄ ስሜት ስለ ተሰማው አይኮነንም፤ ይሄን ስሜት ግን ተከትሎ ወይም አስከትሎ ስለሚያደርገው ነገር ሁሉ ኀላፊነት አለበት፤ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” (ገላ 6፣7) ተብሏልና፡፡

 

አውስቦት ልክ እንደ ኮምፒውተር ክርታስ (ሶፍትዌር) ስንፈጠር በእግዚአብሔር የተጫነ ነው፡፡ ሁልጊዜ የሚከፈት ወይም ጥቅም ላይ የሚውል ግን አይደለም፡፡ አሁንም በኮምፒውተር ዐውድ፣ ከክችሌ (ሃርድዌር) ጋር ተስማምቶ የሚሄድ ነው፡፡ አካል ሳይጠነክር አውስቦትን መለማመድ አይቻልም፤ ዕድሜ ይላል፤ ዐውድ (ጋብቻ) ይላል፤ ሁኔታ ይላል፤ ጊዜ ይላል፤ ቦታ ይላል (ጋብቻ ውስጥ እንኳን በጊዜና ሁኔታ የተከረከመ ነው)፡፡

 

እግዚአብሔር ሰውን ሙሉ አድርጎ ሲሠራው የብዙ ነገሮች ውኀድ አድርጎ ነው፡፡ ይህም ስምረት በሚዛን የሚጠበቅና የሚጸና ነው፡፡ ሁልጊዜ (ሳያቋርጡ) አይበሉም፤ ሁልጊዜ አይተኙም፤ ሁልጊዜ አይሠሩም፤ ሁልጊዜ አይስቁም፤ ሁልጊዜ አይዝናኑም፤ ሁልጊዜም ሩካቤ አይፈጽሙም፡፡ ሕይወት በመለኮታዊ የምጣኔ ሥሪት እንደተበጀ እንደዚያው መመራት አለበት፡፡ አካል አንዱን ክፍል ብቻ አያገዝፍም፤ የአፍንጫ እድገት በጉንጭና አገጭ ካልተመጠነ ተለይቶ ወጣ እንጂ ቅንብብ ውበት አይሆንም፡፡

 

በአውስቦት ውስጥ የታቀደውና የተፈቀደው ስሜት ደስታ ነው፡፡ በጥንቃቄ የተዋቀረ፣ አካልን ከአእምሮ ጀምሮ ያሳተፈና የጊዜ ወሰን የተደረገለት ነው፡፡ ምንም ሥጋ ቢወዱ ከሆዶ በላይ አይበሉ፤ አልያ ቁንጣን ወይም ማንገሽገሽ ይሆናል ውጤቱ! አውስቦትም እንዲሁ ልክ አለው፤ ግጣም አለው፡፡ “ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፤” (መክ 9፣9) ነው የተባለው፡፡ የዕብራይስጡን ቃል ፍቺ ሁነኛ ትርጉም ለመገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ እርካታ ፍጻሜ ነው፤ ከግርጌው ግን ፀፀት ካለበት የተፈቀደ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ ሕሊና ተመልካች ከመሆን አልፎ ተሳቃቂ ከሆነ ድርጊቱ ዐውዱን ለመሳቱ ማሳያ ነው፡፡

 

አውስቦት እና ፀፀት እንዴት ወይም ለምን ተጎራበቱ? ብሎ መጠየቅ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ደንብ ስላልተከበረ፣ ሚዛን ስላልተጠበቀና “በገዛ ሥጋዬ” ስለ ተባለ ነው፡፡ ያለ ሥርዓት ወደ መኖር የመጣ ነገር የለም፤ እንኳን ሕይወት አዛይ፣ ስሜት ተላባሹ ቀርቶ፣ ግዑዙ ዓለምም የራሱ ዑደትና ሕግጋት አለው፡፡ “ሁሉ”ን ያስገኘ እያለ “እንደፈለግን!” አይባልም፤ “ምን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” እንዲሉ ነው፡፡

 

ስሜቱና ግፊቱ፣ ግለቱም ጭምር የአፍታ እብደት ይሆናል፡፡ ረሃቡ ነፍሱን ሊያሳጣው እስኪመስለው ድረስ የከበረውን ነገር በእህል እንዳስለወጠው ዔሳው፡፡ ብዙዎች ክብራቸውን፣ ጥሪያቸውን፣ ሞገሳቸውን፣ ድፍረታቸውን፣ እልቅናቸውንና ከፍታቸውን ቀይረውበታል፣ ለጊዜውም ቢሆን፡፡ ያለ አቻ ግብይት! ሁሉ ሲያልፍ ፀፀትን ተከናነቡ፡፡ ለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ፣ “ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኩርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ” (ዕብ 12፣16) ያለው፡፡ “እንዲህ ልጠግብ በሬዬን አረድኩ!” ነው ያለው ያ ጎበዝ፡፡

 

“ካፈርኩ አይመልሰኝ!” አይሆንም፡፡ የረጠበ ሁሉ አልበሰበሰም፡፡ ወይም ስህተትን ያወልቃሉ እንጂ አይደርቡም፡፡ የሳተ እንዲመለስ፣ ታጥቦ እንዲነፃና አቅም እንዲያሳድግ ነው የሚያስፈልገው፤ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቁጣ የዘገየ ፍቅሩም የበዛ ነው፡፡ እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም” (መዝ 103፣8) አለ በዘመኑ ባልተገባ አውስቦት ከሰገነቱ የተማረከው ዳዊት፡፡

 

አጥር ውበት ነው! የእግዚአብሔርን አጥር አንጥላ፤ አጭር ግን ብርቱ አጥር፡፡ የሚዘለል ግን የማይሸነገል አጥር፡፡ ሁሉ በጊዜውና በወሰኑ ሲሆን ደስታው አይደፈርስም፡፡ ለአንድነት፣ ለእርካታና ለዘር ብዜት የተሰጠውን ስጦታ በአንድ ወገኑ ብቻ አንያዘው፡፡ ደስታችንን የሚወደውን አምላክ በእኛ ሊኖረው የሚገባውን ደስታ ስንከለክለው ቀስ ብሎ (አሰልሶ) ይቆጣል፡፡ ያልባረከውን ደስታ አያቆየውም፤ ያሳጥረው እንደሆነ እንጂ፡፡

 

ከመኝታችሁ በላይ አምላክ ይድላችሁ!

Read 12303 times Last modified on Thursday, 05 February 2015 10:03
Nahu

Nahusenay Afework is a freelance writer and communications consultant. His study at Addis Ababa University earned him MA in Literature. He takes pleasure in writing and consulting people. He is also involved in church ministry in the domain of teaching.

Website: https://www.facebook.com/nahusenay.afework Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 59 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.