በአሁኑ ወቅት በማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ላይ ፣ ካሜራ አስተካክለው አይኖቻቸውን ጨፍነው በከፍተኛ ስሜት በእንባ እየታጀቡ የሚጸልዩ ሰዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል።
እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ ይህ አስቂኝ ድራማ የሚጀምረው ስልኩን አመቺ ቦታ ላይ በማስቀመጥና የቪዲዮ መቅጃውን ቁልፍ በመጫን ነው። ከዚያም ግለሰቡ እራሱን በካሜራው ፍሬም ውስጥ በማስገባት ቀጥሎ ወደ ጸሎት ስሜት ውስጥ ይገባል። አንዳንዴም የሃዘን ሙዚቃን ከጀርባ ይታከልበታል::
ጸሎት ካሜራ ፊት ሲቀርብ ዋናው አላማው እግዚአብሔርን ማነጋገር ነው ወይስ ተመልካቹን መማረክ? በዓይነ ልቦናችን ምንስለው የእውነት ጸሎታችንን የሚሰማንን እግዚአብሔር ወይስ የቀረጽነውን ቪዲዮ ኤዲት አድርገን ጨርሰን ከለቀቅነው በኋላ በየስልክ መስኮቶቻቸው የሚመለከቱንንና “ፐ ጸሎት!” የሚሉንን ተከታዮቻችንን?
ኣረ ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደረስን?
በእርግጥ ይህ አዝማሚያ የመጣው ዝም ብሎ አይደለም። አዲሱ ትውልድ ህይወቱን በሙሉ በማህበራዊ ሚዲያ ማጋራትን እጅግ እየለመደውና የዕለት ዕለት ተግባሩ እያደረገው በመምጣቱ ነው። የበሉትን፤ የተመገቡበትን ምግብ ቤት፤ ውሏቸውን፤ የለበሱትን ልብስ ወዘተ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት እየተለመደ መጥቷል:: ለዚህ ትውልድ ያልተቀረጸና ያልተለጠፈ ነገር እንደ አልተደረገ ይቆጠራል። ታዲያ በስውር ልናደርጋቸው የሚገቡ ወይንም የታዘዝናቸው መንፈሳዊ ተግባራቶችም ከዚህ ተጽዕኖ አላመለጡም። ቀደም ሲል መንፈሳዊ ሕይወት የጓዳ እና የግል ተደርጎ ይወሰድ በነበረበት ልምምድ ውስጥ ለኖርነው፣ አሁን ያለው ግልጽነት እና ሁሉንም ነገር ለህዝብ ማሳየት ትልቅ የባህል ሽግግር መኖሩን ያሳያል።
ቴክኖሎጂ ወንጌልን፤ የእግዚአብሔርን ቃል እና የተረዳነውን እውነት ለሌሎች እጅግ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ቢረዳንም፣ ያሉንን ሁሉ መንፈሳዊ ተግባራቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ማምጣትና ለራስ ትርፍ መጠቀም እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው::
ጸሎት በፈጣሪ እና በሰው መካከል የሚደረግ እጅግ ግላዊ ግንኙነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው…“ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዝጋ፥ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” ማቴዎስ 6:6
ኢየሱስ እየኮነነ የነበረው፣ የሚጸልዩት ሰዎች በሰሚዎች ዘንድ መንፈሳዊ መስለው ለመታየት እንዲችሉ ተብሎ ታቅዶ የሚቀርብን ለራስ ጥቅም የሚውልና ለታይታ የሚደረግ "የቲያትር" ጸሎትን ነው። ዛሬ ምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ማለት የ ቲክቶክና የፌስ ቡክ ልጥፎች እንደማለት ነው::
መጽሃፍ ቅዱስ ላይ በግል ወይንም በስውር እንድናደርጋቸው ከተጻፉ ተግባራት መካከል ሁለቱ ጸሎት እና መስጠት ናቸው። ሁለቱም በስውር ይደረጉ እንጂ ውጤቱ በግልጽ እና በአዳባባይ እንደሚሆን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር በግልጽና በአደባባይ እንደሚከፍለን መጽሃፉ ይነግረናል።
ጸሎት ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ የኃጢአት መናዘዝ፣ ንስሐ፣ ምስጋና፣ አምልኮ፣ ውዳሴ፣ ምልጃ እና ለምሪት ወይም ለሌላ እርዳታ የሚቀርብ ልመና መሆን አለበት። ጸሎት መንፈሳዊ ድራማ ከሆነ፣ እና በእውነት ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ለተመልካቾች እይታ ተብሎ የሚቀረጽ ከሆነ፣ እሱ እውነተኛ ጸሎት አይደለም። ጸሎትን ለሰው ማሳያ (Show-off) አድርገን ማቅረብ የለብንም።
ይህ ቅዱስ የሆነውን ስርዓት ማቃለል እና ጸሎትን ለራስ ዝና መጠቀም፤ ትልቅ ጥፋት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ "ዘመኑ የዲጂታል ነው፣ ወንጌልም በቲክቶክ መሰራጨት አለበት" የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ። ይሁን እንጂ፣ ወንጌልን በማሰራጨት እና ራስን በማስተዋወቅ መካከል ያለው መስመር መለየት አለመቻሉ አሳሳቢ ነው።
አሳየኸኝ ለገሰ "የመጻተኛው ስልክ" በተሰኘው መጽሃፉ “መልካም ሥራዬን እዩልኝ!” በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን ጽፎ ነበር።
“የማኅበራዊ ሚዲያ ምልልሳችን ነገር ከተነሣ፣ በምስሎቻችን ብቻ ሳይሆን በመልካም ሥራዎቻችንና በልዩ በልዩ አገልግሎቶቻችን ምስጋናን ለመቀዳጀት መፈለግ ሌላኛው ወጥመድ ነው። ርግጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የሰፈረ የመልካም ሥራ ገለጻ ሁሉ ለታይታና ለመወደስ የቀረበ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ሌሎችን ለመልካም ሥራ በሚያነሣሣ መልኩ፣ በንጹሕ ኅሊና፣ የተለያዩ በጎ ሥራዎችን ለመከወን ያደረጉትን መልካም አስተዋጽኦ የሚያጋሩን አሉ። ይሁን እንጂ በአንጻሩ እግዚአብሔርን ማእከል ባላደረገና ጠቅመነዋል የሚሉትን ሰው በሚያዋርድ መልኩ፣ የከወኑትን መልካም ሥራ ሁሉ ወደ አደባባይ እያመጡ “ክብር አስገቡ” የሚሉን የስምና የዝና ጥመኞችም አሉ። በጓዳ የተደረገን መልካም ሥራ ሁሉ ለታይታ ማቅረብ ከጌታችን ትእዛዝ ጋራ ፈጽሞ የሚቃረን ነው። መልካም ሥራችንን ሰዎች እንዲያዩት ማቅረብና ሙገሳ መፈለግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋችንን እንደሚያሳጣን ተጽፏል፤ “ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን (አገልግሎታችሁን) በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም” (ማቴዎስ 6፥1)። ይህን ባስጠነቀቀን ጌታ ፊት ስንቀርብና ሥራችንም በሚፈትነው እሳቱ ውስጥ ሲያልፍ በርሱ ዘንድ ዋጋ ቢስ እንዳንሆን ያሰጋል።”
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በቲክቶክ ሁለት ጥንዶች እየጸለዩ ራሳቸውን ቀርጸው ያጋሩትን የተንቀሳቃሽ ምስል ከተመልከትኩ በኋላ ነው። የቪዲዮውን መስፈንጠሪያ የአስተያየት መስጫ ቦታ ላይ አስቀምጥላችሗለሁ::
ያዕቆብ 1:19 ለመስማት የፈጠንን ለመናገርም የዘገየን መሆን እንዳለብን ይናገራል። እነዚህ እውነታዎች በማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ላይም ሊተገበሩ ይገባል። ለመለጠፍ ያለንን ተነሳሽነት (Motive) ሁልጊዜ መመርመር አለብን።
Bereket Tadesse