You are here: HomeSocial Issues እግዚአብሔር ክቡር ጸጋን የሰጠው ለቴክኖሎጂ (ለAI) ሳይሆን በመልክና በምሳሌው ላበጀን፣ በክርስቶስ ደም ለዋጀን ለእኛ ነው::

እግዚአብሔር ክቡር ጸጋን የሰጠው ለቴክኖሎጂ (ለAI) ሳይሆን በመልክና በምሳሌው ላበጀን፣ በክርስቶስ ደም ለዋጀን ለእኛ ነው::

Tuesday, 20 January 2026 12:21
አሁን ሁለት ዓመት ሊሞላው ነው። አንድ ወዳጄ፣ በAI የተቀናበረ መዝሙር "እንዲህም ተጀምሯል" ለማለት በቴሌግራም ልኮልኝ ሰማሁ። በጊዜው ምን እየመጣ እንዳለ ገርሞኝ አለፍኩት። በቅርቡ ደግሞ ከአንድ አንጋፋ መዘምራን አባል፣ በእኔው ተዘምረው የነበሩና አሁን በዚሁ መልክ የቀረቡ ውሱን ዝማሬዎች በዋትስአፕ ተላኩልኝ። አስተያየትም ተጠየቅሁ። ጥቂት አሳቦችን ተለዋውጠን ውይይቱ በየደረጃው መቀጠል አለበት በሚለው ቋጭተናል። የእኔ አስተያየት የሚከተለው ነው፦
 
  1. በAI "እየተዘመሩ" ያሉ መዝሙሮች በተወሰነ ደረጃ በአድማጭ የመደነቅ አቅም አላቸው። የሙዚቃ ቅንብራቸውም ሆነ የዜማ ቅላጼያቸው ሳቢ ሊሆን ይችላል። እንዳየሁት፣ ከዋናው original ጋር ለመመሳሰል በጣም የተጠጋ ነው። እስከ ሰማሁት ድረስ ግን፣ አልፎ አልፎ የቃላትና የፊደላት ግድፈት ይስተዋልበታል። የዜማም እንደዚሁ። አንዳንድ ቦታ ላይ የሚደመጠው መኮላተፍ የፊደላት ድምጽ ያላግባብ መጥበቅና መላላት ሰሚውን "ያዝ" ማድረጋቸው አይቀርም።

  2. የቅንብሩና የቅላጼው "ማማር" ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃል አንድ ነገር አስታውሶኛል። የሚያምር ነገር የራሱ መልካምነት ሊኖረው ይችላል። ሁሉም ግን ጉዳት አልባ ይሆናል ማለት አይደለም። በኤድን ገነት እነ አዳም የበሉት ፍሬ የሚያምር ነበረ። "ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።"(ዘፍጥ 3:6) መብሉ ማራኪና አስደሳች ቢሆንም ጉዳትን ያስከተለ ሆኗል። መንፈሳዊ ግንኙነትን አቋርጧል። የሚጣፍጥ መጠጥ ሁሉም ለጤና ይጠቅማል ማለት አይደለም። በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 23 ላይ መልኩ በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ ... የሚለውም ታወሰኝ።(ምሳ 23፡31-32) ይህ ሁሉ ለውሳኔና ለእርምጃ ሳንቸኩል፣ የአዳዲስ ነገሮችን ጥቅምና ጉዳት ለማጥናት ጊዜ መውስድ እንደሚኖርብን ይመክረናል።

  3. እግዚአብሔር አምልኮን እንዲያቀርቡለት ያዘዘው ሕያዋን ሰዎችን (እኛን) ነው። AI ድምጹ የሰውን ይመስላል እንጂ ሰው አይደለም። እኛን ተክቶ እንዲዘምር፣ እንዲያመልክና እንዲጸልይ፣ መደረግ የለበትም። በእርግጥ፣ ድንጋይን ጨምሮ ግዑዝ ፍጥረተ ዓለምም የፈጣሪውን ክብር ይናገራል። ይህ እውነት ነው። (መዝ 19:1-4) እርሱም ቢሆን ሰው ሰራሽ አይደለም።

  4. በበጎ ጎኑ፣ ሰው በሠራው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ድምጽና ምስልን አባዝቶና አጉልቶ መልዕክትን ወደ ሩቅ ሳይቀር ማድረስ የቆየንበትና ያለንበት እውነታ ነው። ይሁንና፣ ቴክኖሎጂ መልዕክተኛን አጋዥ እንጂ መልዕክት ፈጣሪ (ደራሲ) አልነበረም። እጅግ መጠንቀቅ የሚገባን እዚህ ላይ ነው። እግዚአብሔር ክቡር ጸጋን የሰጠው ለቴክኖሎጂ (ለAI) ሳይሆን በመልክና በምሳሌው ላበጀን፣ በክርስቶስ ደም ለዋጀን ለእኛ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።

  5. በተሰጠን ጸጋ ለማገልገል በጸሎትም በዝግጅትም መትጋት አቁመን፣ የሰው ወለድ ጥበብ ጥንቁቅ ተጠቃሚዎች ከመሆን ይልቅ፣ ፍጹም ጥገኞችና ምስኪን ሰነፎች ተደርገን እንዳንቀርም በጥልቀት ልናስብበት ይገባል።
AI መስመር ተበጅቶለት ከጥንቃቄ ጋር ብንጠቀምበት ይበጃል የሚል ጥቅል አሳብ እንዳለም እረዳለሁ። ጥያቄው ምን ዓይነት መስመር በማን ይበጅ? የሚል ነው። እግዚአብሔር ማስተዋልንና ክእርሱ ጋር ያለንን ሕብረት የምናጠብቅበትን ጥበብ ይጨምርልን። በደህናም ያሰንብተን።
 
በክርስቶስ ፍቅር
ዘማሪ ተስፋዬ ጋቢሶ
Read 36 times Last modified on Tuesday, 20 January 2026 12:39
Pastor/Singer Tesfaye Gabiso

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 220 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.