ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው "የቲክቶክ ሽልማት" ፕሮግራም በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። መነጋገሪያ የሆነው ግን በሽልማቱ ወይም በቲክቶከሮቹ ስራዎች ጥራት ላይ ሳይሆን፤ የሽልማት መርሃግብሩ ላይ በታደሙት ወጣቶች (Titokers) አለባበስ እና አቀራረብ ነበር። ያየነው ነገር “የሄ ሁሉ እየሆነ ያለው ይህቺ ያደግንባት እማማ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይ?" የሚያሰኝ እና እጅግ የሚያስደነግጥ ክስተት ነበር።
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ እጅግ የከበረ፣ የተዋበ እና ዓለም የሚያደንቀው አለባበስ ያላት ሀገር ናት። ይሁንና በዚህ መድረክ ላይ የተመለከትነው ግን ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነት (Decency) ጋር ፍጹም የተጣላ ነበር። ወጣቶቹ የለበሱት ልብስ የአሜሪካን የሆሊውድ ተዋንያን በ "Met Gala" ወይም በሙዚቃ ሽልማቶች ላይ የሚለብሱትን፣ አካልን የሚያጋልጡ እና ለባህላችን እንግዳ የሆኑ "ኮስቲውሞችን" ነበር። ሀበሻዊ ውበት ጠፍቶ፣ ምዕራባዊ የማስመሰል (Imitation) አባዜ ጎልቶ ታይቷል።
ጋሽ ንጉሴ በእንድ “የአገር ያለህ!”: በሚል መጣጥፉ የሚከተልውን ጽፎ ነበረ…
“የአገራችን ሕሊናዊ በር ለሁሉም ክፍት ሆነ፡፡ በፍርሃት ይሁን በድንቁርና በጀብደኝነት ይሁን በአርቆ አስተዋይነት ለብዙ ዘመናት መክተን ያያዝነው መዝጊያችን ገርበብ ብሎ ሳይሆን ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁን ወልጋዳም ጎፋፋም፣ ሃምሳ ቀንድ ያበቀለም ጭራቅ እንዳይገባ የሚከለክል ምንም ዘበኛ የለም፡፡ ደግሞ ለክፋቱ በገፍ የሚገባው የተቃናው የለዘበውና የተገራው ሳይሆን ጉዳጉድ ግሳንግሡ ነው፡፡
ድንበራችንን ዘልቆ ሲገባ በእንግዳ አክባሪ ባህላችን ተሳስቀን ተቀብለነው አገሩን ይሄዳን ስንል እዚሁ ተንፈራጥጦ ተቀመጠ፡፡ ጭራቁ ሁሉ ቤተኛ ሆነ፡፡ ለመሆኑ እዚህ አገር ክፉ አስተሳሰብና ዝቃጭ የሥነምግባር አተላ እንዳይደፋ የሚከለክል ሃይ ባይ ይገኛል?
ገበያው ላይ ያለው ዕቃና አገልግሎት ብቻ በሆነ ኖሮ እጅግም አያሳስብም ነበር፡፡ አሁን ግን እየተሸጠ፣ እየተሸመተም ያለው የአስተሳሰብ ዐይነትና የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡ ከዚሁም አብዛኛው መሠረታውያን የሆኑትን የስብእና ማልሚያ እምነቶች የሚንድ፣ ሠናያት ምግባራትን የሚያኪያኪስ፣ መለኪያ የለሽነትን የሚያራግብ፣ እብደትን የሕይወት ፈርጥ አድርጎ የሚሳይ፣ የሞራል ልቅነት ሲያይ ብራቮ! እያለ የሚያጨበጭብ፣ ከማኅበረሰብ ጤና ይልቅ ፈንጠዝያን የሚያከብር፣ አዳዲስ የርኩሰት አራዊት የሚያራባ የክፋት ሸቀጥ ነው፡፡
ዓለሙ ሁሉ በእብደት ሲሮጥ የቀደመን ስለመሰለን እነሱ በሶምሶማ የሚሄዱበትን ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያን በሽምጥ ጋልበን ደረስንበት፤ በአንዳንድ በኩል እንዳንቀድማቸውም ያሰጋል፡፡ መለኪያ የለሽነት ልክ ሆነ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ይህ ነጭ፣ ይህ ጥቁር ማለት ይቻል ነበር፡፡ “ኧረ ነውር ነው!” ሲባል አዎ ነውር ነው ይባል ነበር፤ ወይም ቢያንስ መሬት መሬት እያየን ፀጉር እያሻሸን እንለማመጥ ነበረ፡፡ ክፋት ዛሬ የተፈጠረ ባይሆንም በስሙ ተጠርቶ ክፉ ይባል ነበር፤”
በጣም የሚያስፈራው ነገር የክስተቱ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ የህብረተሰቡ እሴት (Values) እንዴት እየተሸረሸረ እንደሆነ ማየቱ ነው። ድሮ "ነውር" የሚባለው ነገር ዛሬ "ዘመናዊነት" ተብሎ ስም ወጥቶለታል። ወጣቱ ትውልድ ስልጣኔን የሚለካው ማንነቱን በመጣል እና የሌላውን በመልበስ ከመሰለው አደጋ ላይ ነን። እራቁትን መሄድ እና እንግዳ የሆኑ ልብሶችን መልበስ እንደ "Art" ወይም "Fashion" መቆጠር ከጀመረ ሰንብቷል። ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ የሞራል ልልላትን (Moral decay) እያስከተለ ነው።
ባጠቃላይ፣ ይህ የቲክቶክ ሽልማት መድረክ የደወለልን ደወል ቢኖር፣ ባህላችን በምን ያህል ፍጥነት እየተቀየረ እና እየጠፋ እንደሆነ ነው። ወላጆች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሚመለከተው አካል ሁሉ ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል። ዘመናዊ መሆን ይቻላል፤ ነገር ግን ዘመናዊነት መሠረትን እና ማንነትን በመጣል ሊሆን አይገባም።
ከትዕይንቱ በስተጀርባ ያለው ስውር እጅ
ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የቲክቶክ ሽልማት ፕሮግራም ላይ ያየነው ነገር የባህል መውረር ብቻ አይደለም፤ ከዚያ በላይ የሆነ ጥልቅ መንፈሳዊ አንድምታ አለው። በ"ሬድ ካርፔት" ላይ የተመለከትነው እርቃንነት እና የምዕራባውያን አምልኮ፣ ከፋሽን አልፎ የዚህ ዘመን ክፋት ምን ያህል እንደገነፈለ ማሳያ ነው።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የቲክቶክ ሽልማት ፕሮግራም ላይ ያየነው ነገር የባህል መውረር ብቻ አይደለም፤ ከዚያ በላይ የሆነ ጥልቅ መንፈሳዊ አንድምታ አለው። በ"ሬድ ካርፔት" ላይ የተመለከትነው እርቃንነት እና የምዕራባውያን አምልኮ፣ ከፋሽን አልፎ የዚህ ዘመን ክፋት ምን ያህል እንደገነፈለ ማሳያ ነው።
እንደ ክርስቲያን መንፈሳዊ ዓይናችንን ገልጠን ልናይ የሚገባን እውነት አለ። ይኸውም ከእነዚህ ልጆች በስተጀርባ፣ ትውልዱን ከእግዚአብሔር እውነት ለማራቅ ሌት ተቀን የሚሰራ ጠላት መኖሩን ነው። ዲያብሎስ ልጆቻችንን ለመውጋት የሚጠቀምበት ስልት ረቂቅ ነው። በቀጥታ "ሰይጣንን ተከተሉ" አይላቸውም። ይልቁንም እነዚህን በቲክቶክ ላይ የሚታዩ ታዋቂ ግለሰቦችን በመጠቀም፣ ኃጢአትን እንደ "ዘመናዊነት"፣ እርቃንነትን እንደ "ውበት"፣ እና እግዚአብሔርን አለመፍራትን እንደ "ነጻነት" አድርጎ ያቀርብላቸዋል። ዓላማው የልጆቻችንን አእምሮ መቅረጽ (Shaping the mind) ነው። አንድ ጊዜ አእምሯቸው ለኃጢአት ከተመቻቸ እና የውሸት ነጻነትን ካመነ፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይጣላል።
እንደ ክርስቲያን ወላጅ ምን እናድርግ?
እንደ ክርስቲያን ወላጅ፣ እየሆነ ያለው ሁሉ መራራ ቢሆንም ልንውጠው የሚገባ አንድ እውነት አለ። ብንወድም ባንወድም፣ እነዚህ ቲክቶከሮች ወይም "ኢንፍሉዌንሰሮች" በልጆቻችን እና በመጪው ትውልድ ላይ ያላቸው ተጽእኖ እጅግ የላቀ ነው። ልጆቻችን እኛን ከመስማት እና ከእኛ ከመማር ይልቅ፣ እነዚህን የቲክቶክ ታዋቂዎች ማየት፣ ማድነቅ እና መከተልን ይመርጣሉ።
በሰንበት ትምህርት ቤት ከሚማሩት ይልቅ ወይም በቤት ውስጥ ከምንመክራቸው ይበልጥ፣ በቲክቶክ ላይ በሚያዩት ቪዲዮ ባህሪያቸውን ከምናስበው በላይ ይቀረጻል። ልጆቻችን እነዚህን ሰዎች እንደ "ጀግና" እና "ምሳሌ" (Role Models) አድርገው ነው የሚመለከቱት። እነርሱ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ "ትክክል" እና "ዘመናዊነት" መስሎ ስለሚታያቸው፣ ሳያውቁት የእነርሱን ማንነት ይላበሳሉ።
እኛ ስለ ጨዋነት እና ስለ እግዚአብሔር ፍርሃት አንድ ሰዓት ብንሰብክ፣ እነሱ በ30 ሰከንድ ቪዲዮ የልጆቹን ልብ የመስረቅ አቅም አላቸው። ዲያብሎስ ይህንን የሚዲያ ኃይል ተጠቅሞ የልጆቻችንን ማንነት እየቀረጸ፣ ለእግዚአብሔር የማይመች ትውልድ እያዘጋጀ ነው። ዝም ብለን እይናችን እያየ የምንተወው ጉዳይ አይደለም፤ ጦርነቱ በልጆቻችን በአእምሮ ላይ ነው።
እና ምን እናድርግ?
ትግላችን "ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን" ከጨለማ ገዢዎች ጋር በመሆኑ የሚከተሉትን መንፈሳዊ እርምጃዎች መውሰድ አለብን፡
- የቤታችንን "በር" መጠበቅ፦ ዓይን የልብ መግቢያ በር ነው። ልጆቻችን በስልካቸው ስክሪን ምን እንደሚያዩ መቆጣጠር፣ መከልከል ወይንም መገደብ
- የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ማልበስ፦ ልጆቻችንን በቃሉ እውነት ካላስታጠቅናቸው፣ የዓለም ማዕበል ጠራርጎ ይወስዳቸዋል። የዚህ ዓለም ከንቱነትን በልባቸው እለት እለት መቅረጽ አለብን።
- በጸሎት መትጋት፦ ይህ መንፈሳዊ ጦርነት ስለሆነ፣ ለልጆቻችን አእምሮ አጥብቀን መጸለይ ግዴታችን ነው። ዲያብሎስ ዕለት በዕለት በነዚህ ሚድያዎች የሚረጨውን መርዝ በጸሎት እና በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው ማርከስ የምንችለው።
- የእኛን ህይወት አይተው እግዚአብሔርን እንዲወዱ በትጋት ምሳሌያዊ ህይወት ኖሮ ማሳየት፦ የዓለም ብርሃንና ጨው መሆናችንን በተግባር በማሳየት፣ ልጆቻችን ከቲክቶክ ኮከቦች (Stars) ይልቅ በእኛ ህይወት በሚገለጠው በክርስቶስ ብርሃን እንዲማረኩ ማድረግ ይጠበቅብናል።
እግዚአብሔር ይርዳን!