You are here: HomeSocial Issues ሲ.ኤስ ሉዊስ እና ኮሮና ቫይረስ

ሲ.ኤስ ሉዊስ እና ኮሮና ቫይረስ Featured

Written by  Wednesday, 18 March 2020 07:01

እንግዲህ፥ ኮሮና (COVID-19) እጅግ ከባድና ገዳይ ዓለማቀፍ ወረርሽኝ መኾኑ በዓለም ጤና ድርጅት ከተረጋገጠና ከታወጀ ሰንብቷል። በመኾኑም፥ ማንኛውንም የጥንቃቄ እርምጃዎች ኹሉ መወሰድ ይኖርብናል። ተገቢው ነገር ጥንቃቄ እንጂ ሥጋት አይደለም። ቫይረሱ ያደረሰውንና ሊያደርስ የሚችለውን ጕዳት በማምሰልሰል ልክ ባጣ ፍርኀትና ጭንቀት መርበድበድ አይኖርብንም። ጭንቀት ለነገአችን አንዳች ባናተርፍበትም የዛሬን ሰላማችን ግን ይነጥቀናል። እያንዳንዱ ቀንና ዘመን የየራሱ ሥጋትና ጭንቀት ተሸክሟልና።

 

የዛሬ 72 ዓመት አካባቢ፥ አቶሚክ ቦምብ ዓለማቀፋዊ ስጋት በደቀነ ጊዜ፥  ሲ. ኤስ. ሉዊስ የተናገረው ነገር ለእኛ ዘመን የሚኾን ሐሳብ ይዟል። ከሉዊስ አባባል ለመማር እንድንችል፥ “አቶሚክ ቦምብ” የሚለውን “ኮሮና ቫይረስ” በሚለው ብቻ ለውጣችሁ አንብቡት።

 

ሉዊስ እንዲህ ይናገራል?

 

በአንድ በኩል ስለ አቶሚክ ቦንብ ልባችን እስኪወልቅ በሐሳብ እንናጣለን። “በአቶሚክ ቦንብ ዘመን እንዴት ነው መኖር ያለብን?” እንላለን። መልካም፤ እኔ ደግሞ እንዲህ ብዬ እንድመልስላችሁ እገደዳለሁ። “በዐሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት የለንደን ከተማን ዓመታዊ የወረርሽኝ መቅሰፍት ያናውጣት በነበረበት ዘመን ልትኖሩ ትችሉ እንደ ነበረው፤ ወይም፥ በቫይኪንጎች ዘመን ጨካኝ ዘራፊዎች ከስካንዲኔቪያ አካባቢ በቍጣ እያረገረጉ መጥተውባችሁ በማንኛውም ውድቅት ሌሊት ጕረሯችሁን በጥሰውት በሚኼዱበት አስፈሪ ዘመን ልትኖሩ ትችሉ እንደ ነበረው፤ ወይም፥ በርግጠኛነት፥ በዘመነ ካንሰር፥ በዘመነ ቂጥኝና ጨብጥ፥  በዘመነ ልምሻ፥ በዘመነ የአየር ወረራ፥ በዘመነ የባቡር አደጋ፥ በዘመነ የመኪና አደጋ ወዘተ… ልትኖሩ እንደቻላችሁት ዛሬም ኑሩ” በማለት እመልስላችኋለሁ።

 

በሌላ አባባል፥ ያለንበትን ኹኔታ ታይቶ የማይታወቅ ብርቅ-ጭንቅ አድርገን በማጋነን አንጀምረው። የተወደዳችሁ ክቡራንና ክቡራት፥ እመኑኝ፤ እናንተም ኾናችሁ የምትወዷቸው ሰዎች ኹሉ ከአቶሚክ ቦምብ የፈጠራ ውጤት በፊት ትሞቱ ዘንድ ፍርድ የተላለፈባችሁ ናችሁ። ከሰብአውያን ፍጡራን መካከል፥ በመቶኛ ስሌት፥ እጅግ ብዙዎቻችን ደስ በማያሰኙ (ዘግናኝ ላለማለት) መንገዶች ነው፥ ቅጥባችን በደረሰ ጊዜ፥ የሞት ጽዋችንን የምንጐነጨው። በርግጥ ከቅድመ አያቶቻችን ይልቅ በጣም ተጠቃሚ ያደረገንን ነገር አግኝተናል—ሕመም ማደንዘዣ (anesthetics) ይባላል። እሱ ደግሞ አኹንም አለን።

 

እናሳ? ቀድሞውንም ቢኾን ከበርካታ የመሞቻ ዕድሎች ጋር ለተፋጠጠውና ሞት ራሱ ያጋጣሚ ዕድል ሳይኾን አይቀሬ ዕጣፈንታው ለኾነበት ዓለም ሳይንቲስቶች ሕይወትን በሥቃይና በለጋነት የሚቀጥፍ አንድ ተጨማሪ የመሞቻ ዕድል ለዓለማችን ጨምረው ፈጠሩት ብለን በልቅሶና ሣግ ማንሾኻሾክና ፊታችንን በኀዘን መዘፍዘፍ ልግጫ እንጂ ሌላ ምን ይሉታል።

 

ልናሠምርበት የሚገባው የመጀመሪያው ነጥብ ይኸ ሲኾን፥ ልናደርገው የሚገባ የመጀመሪያ ተግባራዊ እርምጃችን ደግሞ እርስ በርሳችን በአንድነት መሰባሰብ ነው። ኹላችንም በአቶሚክ ቦንብ ሙጥጥ ተደርገን የምንደመሰስ ቢኾን እንኳ ትርጕም ያለው ሰብአዊ ግብሮቻችን እየፈጸምን—ማለትም፥ በጸሎታችን እየተጋን፥ ሥራችንን እየከወንን፥ እያስተማርን፥ እያነበብን፥ ሙዚቃችንን እያዳመጥን፥ የልጆቻችንን ሰውነት እያጠብን፥ ቴኒሳችንን እየተጫወትን፥ ከወዳጅ ጓደኞቸችን ጋር እየተወያየና እየተጨዋወትን፥ […] ሳለን ይሟጠን፤ በፍርኀት በርግገውና እርስ በርስ ተፋፍገው በጋጣቸው እንደ ተመሰጉ በጎች ስለ ቦንብ ጥፋት እያሰብን፥ በፍርኀት እየራድንና በሥጋት እየተንቀጠቀጥን በሠቀቀን የምንቀቀል አንኹን። ቦንብ ምን ያደርገናል? ቦምብማ ሥጋችንን ያፈርሰዋል። (በርግጥ ማንኛውም ጥቃቅን ተሕዋስያን ያንን ያደርጉታል።) ቦንብ ሥጋችንን የማፍረስ ጕልበት ቢኖረውም ቅሉ፥ አዕምሯችንን ሊነግሥበትና ሊቈጣጠረው ግን አይገባውም።

 

— “On Living in an Atomic Age” (1948) in Present Concerns: Journalistic Essays

Read 2602 times Last modified on Wednesday, 18 March 2020 22:43
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 55 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.