You are here: HomeSocial Issues “ተያይዘን እንዳንወድቅ”…

“ተያይዘን እንዳንወድቅ”… Featured

Written by  Thursday, 04 October 2018 01:59

የዘመን ክፉ

 

ዘመኑ ክፉ ነው። ዘመኑን ያከፋው በክፉ ሰዎች ስለ ተሞላ ይመስለኛል። በዓለማችን ልዩ ልዩ አቅጣጫዎች የምናየውና የምንሰማው ዜና እጅግ የሚያሠቅቅ ኾኗል። ጽንፈኝነት ተስፋፍቷል። የጥላቻና የምሬት ቅስቀሳዎች ሰላም እያደፈረሱና ዕልቂት እየወለዱ ነው። ግለ ሰባዊ እንካ ቅመሶች እና ዐምባጓሮዎች ተባብሰዋል። ማኅበረ ሰባዊ ብጥብጦች በብዛትም በስፋትም ጨምረዋል። ዐይነታቸው ብዙ መጠናቸውም አስፈሪ የኾኑ ፖለቲካዊና ባህላዊ ቀውሶች ተበራክተዋል። ግጭትና ፍጅት፥ ሰቆቃና ዋይታ፥ አድልዎና መፈራረጅ፥ ጥላቻና ነገረኛነት ተስፋፍቷል። ጥፋትን በጥፋት፥ ጥላቻን በጥላቻ፥ ስሕተትን በስሕተት ለማረም የሚኳትኑ ሰዎች በዝተዋል። በዝተዋል ብቻ ሳይኾን ሕዝቦችን ለሥጋትና ፍርኀት አጋልጠዋል።

 

ሰው ከራሱም ከሌላውም ጋር የተጣላ ይመስላል። ቂምና በቀል የተንሰራፋባቸውና ጥላቻ የነገሠባቸው ማኅበረ ሰቦች ሞልተዋል። ጥላቻ የጠብ፥ የቅራኔ፥ የሁከትና የመቈራቈስ መንሥኤ እንደ መኾኑ፥ የሰው ሕይወት እየቀጠፈ፥ አገራትን እያናቈረ፥ ሕዝቦችን እያፋጀና ማኀበራዊ ትስስሮችን እየበጣጠሰ ይገኛል። ውክቢያ፥ ዉካታ፥ ብጥብጥና ትርምስ የዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን ዕለታዊ አርእስተ ዜናዎች ናቸው። አርቆ አስተዋይነት የጐደላቸውና በዐመፅ መንፈስ ናላቸው የተበጠበጠ ግለ ሰቦችና ቡድኖች በግልጽም ኾነ በስውር የሚያሽከረክሩት ትውልድ የሚኖርበትን ዓለምና ሕዝብ እያወከ ይገኛል።

 

ሥጋት ያንጃበበበት ዓለም

 

ጀብደኝነት ጥበብ የጐደለው የትዕቢት እብደት ነውና፥ ጠብን እንደ ቋያ እሳት ያቀጣጥላል። አንዱ ለሌላው የማይተኛ እየኾነ መታየቱ የምር ያስጨንቃል። ጭቈና፥ ምዝበራ፥ ጭቅጭቅና ዐምባጓሮ እየተበራከተ መኼዱ አሳሳቢ ኾኗል። አንዳንዶች በደረሰባቸው ጥቃት አቂመው የበቀል ብድር ለመክፈል ጥቍር ደም በማነፍነፍ ላይ ናቸው። ጥላቻ፥ ክፋት፥ ግጭት፥ አለመደማመጥ፥ ብጥብጥ ወዘተ. በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት፥ በየቦታው በየኹኔታው ስለ መዛመቱ እናውቃለን። ሥጋት ያላንጃበበበት የዓለም ክፍል የለም፤ ቢኖርም ትንሽ ነው። የሰው  ልጅ ደም በትንሽ በትልቁ ሰበብ እንደ ጅረት እየፈሰሰ በመኾኑ ጸጥታና ሰላም ከምድራችን ርቀዋል። ዓለማችን በጠና ታማለች፤ ታውካለችም። በሚያስጨንቅ ዘመን ውስጥ ገብተናል።    

 

የምንለው ችግር በሩቅ በሚገኙ ወገኖች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይኾን በእኛው ፊትም የተደቀነ ነው። ወደድነውም ጠላነው በተመሳሳይ ኹኔታ አገራችን ታማለች። ነገሩን ሸፋፍነን ልናልፈው በሞከርን ቍጥርም እየባሰበት መኼዱ አልቀረም። ከበደል አዙሪት መውጣት ተስኖናል፤ የክፋት ሰንሰለቶችም የሚበጣጥሳቸው አልተገኘም። ከሥጋትና ፍርኀት ነጻ አይደለንም። በእውነት እንነጋገር ከተባለ በጽኑ ታመናል። ችግር ላይ ነን። አልታመምንም ብሎ የሚሞግተኝና ጤና መኾናችንን በተጨባጭ ማስረጃ የሚያሳይ ሰው ቢገኝ ንስሓ ልገባ ዝግጁ ነኝ፤ አለመታመማችን እውነት ኾኖ እኔ ብሳሳት እመርጣለሁ።

 

ብዙዎች ተገንዝበውታል ብዬ እንደምረዳው፥ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ምኅዳሩ መታወክ ገጥሞታል። የፖለቲካ ተዋንያኑ የአጨዋወት መንገድ እንከን የሚታይበት እንደ መኾኑ ፍርኀት፥ ጥርጣሬ፥ አለመተማመንና ንትርክ በዝቶበታል። በ2006 . . በታተመው የትሩፋን ናፍቆት በተሰኘ መድበል ውስጥመንገዱም ቢጠብ፥ ጠብን እንጠብየምትል መጣጥፍ አለች። በመጣጥፏ ውስጥ ከተባሉት ነገሮች መካከል የሚከተለውን አንቀጽ እንዋስ፤ እንዲህ ይነበባል።

 

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡድኖች መካከል የሚታየው ፍጥጫ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙና ተመሳሳይ ዜግነት ያላቸው ወንድሞች መኾናቸውን እንድንጠረጥር የሚገፋፋ ነው። ከጥላቻና ከበቀል አዙሪት መውጣት ተስኗቸው ፖለቲካዊ ፉክክርን በጠላትነት በመተርጐም [እርስ በርስ] ተፋጠዋል። በየማኅበረ ሰቡ ውስጥ የተወተፉ የትውልድ እንግውላዮች በበኩላቸው፥ በዘመን ደመና ውስጥ ሰርጎ የተሰወረ ቍስል እየጐረጐሩ ሊያመግሉ ሥንጥራቸውን አሹለው ቆመዋል። እርስ በርስ [ለመተላለቅ] “ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡቀላል ቍጥር የማይሰጣቸው የጠብ አባቶች ከብበውናልና የጠብ ምሳሌ ፍለጋ ሩቅ መዋተት አያስፈልገንም። [1]

 

ችግርማ አለ። አፍንጫችን ሥር የተጐለተ ችግር አለ። ዐይናችንን ጨፍነን ምንም አይታየንም ካላልን በቀር በአስፈሪና አሳፋሪ መፋጠጥ ተከበናል። በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ያልቻሉ ልሒቃን፥ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ፥ ያገኙትን የጠብና የጥላቻ ትቢያ ባገኙት ኹሉ ላይ እየበተኑ ነው። ለአንዳንዶች የተጋነነ መስሎ ቢታያቸውም እንኳ በተወሳሰቡ ኹኔታዎች መካከል እየዳከርን ለመገኘታችን ምስክሮቹ እኛው ነን። አገራዊ ግጭትና ትርምስ ሊያስከትሉ የሚችሉ መሰናክሎች ተደቅነውብናል።    

 

ማናችንም እጃችንን አጣጥፈን የሚኾነውን ኹሉ በትዝብት መመልከት አንችልም። ይህ የነብሩስ ሊ፥ የነሽዋዚንገር፥ የነብራድ ፒትተምኔታዊ ዓለምና ምናባዊ ቅጥቅጥ አይደለም። ፍጥጫው የሰው ልጆች ነው፤ እንደ እኛው ዐይነት ሕያዋን ፍጡራን ናቸው የተቀያየሙት። የአንድ እናት ልጆች ናቸው ቂም የቋጠሩት። ሰዎች ናቸው ደማቸው የሚፈስሰው። እየከፋ ከሔደም የጋራ አገር ነው የሚፈርሰው።

 

ወገኖች ሆይ፥ የጥላቻና ብጥብጥ እሳት እየተንበለበለ አይደልምን? ወደ አምላክ ለመጮኽም ኾነ እንደ ሰው የሚጠበቅብንን የመፍትሔ ፍለጋ ጥረቶች ለማድረግ ከዚህ በላይ የት ድረስ መበጣበጥ አለብን? ችግሩ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለትና እየተባባሰ ከኼደ ማናችንም ከቅራኔው ወላፈን ማምለጥ አይቻለንም።

 

የጠብ ጽልመት ዐብሮነታችንን በኀዘን ማቅ ሊከድነው እያደባ ባለበት በዚህ ወቅት፥ በፀጕር ስንጠቃ ዐይነት ንግግራችንን ለማሳመር መሞከር መፍትሔ አይኾንም። ችግሩ እንደ ኾነ በየሰፈራችን አድፍጧል። በየልቡናችን ጐድቧል። ጥላቻና ቂም ሥር እየሰደደ ነው። ከመወያየት ይልቅ መፈራረጅ ባህል ኾነ። ከመደማመጥ በላይ ጀብደኝነት ተወደሰ። ለችግሮቻችን ኹነኛ መላ ከመሻት ይልቅ የቂም በቀል አዙሪት ናላችንን በጠበጠው። ገጣሚ ነቢይ መኰንን፥ ይህን ማኅበረ ሰባዊ ደዌ ልንገላገለው ከምንችልበት ምኞት ጋር ግብ-ግብ ገጥሞ ይመስላል፥ እንዲህ ሲል ያምጣል፤

 

መች ይበጠስ ይኾን፥ ይህ የቂም ሰንሰለት? 
ይህ የቂም ጕማሬ፥ ይኼስ የቂም ዑደት 
መች ይኾን አገሬ፥ ልጅ የሚወጣላት? 
ቂም አርጅቶ ሞቶ፥ ሰው የሚኖርባት

በቀል ሬሳው ወጥቶ፥ ሰው የምንኾንባት። [2] 

 

በርግጥ መች ይኾን? ሕመማችንና መዘዙን መጠየቅ አስፈልጎናል። አዎን፥ ታመናል። ለመደማመጥ የማይችሉና የማይፈልጉ ታዳጊዎች በጠብ አባቶች እየተመሩ ጽንፍ ለጽንፍ በማሸብሸብ ላይ ናቸው። ቂመኞች ጨክነዋል፤ ስድብ፥ ዛቻና ማስፈራራት ነግሧል። የእምነት አባቶችመንፍቀዋል ውሸት ባህል ወደ መኾን እየተለወጠ ይመስላል። መማር ለማኅበረ ሰባዊ ለውጥ፥ ፍትሕ፥ ነጻነትና አገራዊ መተባበር ወደ ፊት መራመድ ነው ወይስ እንጣጥ ብሎ ወደ ኋላ መዝለል አስብሏል። ተምህሯዊ ሴሰኝነት አገር ምድሩን በክሏል፤ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን እውነትን ከመናገር ጾመዋል፤ አንድም አንደበታቸው ጐድፏል፤ አንድም ብርዓቸው ታጥፏል። ኹኔታው የእውነት ያስፈራል።

 

በጕዳዩ ላይ ጥናታቸውን አድርገው በቅርቡ በታተመው መጽሐፋቸው ያስነበቡት / ጠና ደዎ እንደሚያሳስቡት ሥጋቱ ጥልቅ ይመስለኛል፤

 

ዛሬም በፖለቲካው ረገድ በነበረው ክፋት ላይ ሌላ ዐዳዲስ ክፋቶች እየተጨመሩ ናቸው። ኹኔታዎች ኹሉ በነበረው መልካቸው የሚቀጥሉ ከኾነ ከዚህ በፊት ካደረግነው በላይ ዕጥፍ ድርብ ዋጋ ለመክፈል እንገደድ ይኾናል። በዚህ ምክንያት ዛሬም ዜጎች ይሠጋሉ። ሥጋታቸው ደግሞ ስለ ብዙ ነገር ነው። ለግል ሕይወታቸው ይሠጋሉ፤ ስለ አገራቸው ደኅንነትና ሰላም ይሠጋሉ፤ ዛሬ ስላለውና ወደፊት ስለሚኖረው ይሠጋሉ፤ ሥጋቱ ትክክለኛ ሥጋት ነው። [3] 

 

ሥጋቱ እውነት ነው። የሥጋቱ ሰበብም ብዙ ነው። የበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውጤት መኾኑም አከራካሪ አይደለም። የከበበንን ሥጋትና ፍርኀት ሳውጠነጥን ከሚታሰቡኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባባት አንዱ ይኸውና። በእርሱ እንንደርደር። የእስራኤል ታሪክ አንዱ ገጽ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው

 

በሰይፍ የተጨባበጡ ወንድሞች

 

ሳኦልና እርሱን የተካው ዳዊት በቅደም ተከተል በእስራኤል ላይ ነግሠው ነበር። ባለመታዘዙ ምክንያት እግዚአብሔር የናቀው ሳኦል እርሱን ለመተካት እግዚአብሔር በቀባው ዳዊት ላይ ጥርስ ነክሶበት ከረመ። በዚህም ምክንያት፥ ዳዊት የእግዚአብሔር ቀን እስኪደርስ፥ በየጫካውና ምድረ በዳው እየተንከራተተ ለመኖር ተገደደ። ሳኦል፥ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት እግዚአብሔር እንደ ተለየው በዙፋን ላይ ከቈየ በኋላ በጊልቦዓ ኮረብታ ላይ አይሞቱ ሞት ሞተ (1ሳሙ. 31) በዚያን ቀን ጊልቦዓ በሳኦል ደምና በዳዊት እንባ ታጠበች። ምንም እንኳ ሳኦል ዳዊትን ቁም ስቅሉን ሲያሳየው የቈየ ቢኾንም፥ የሳኦል ሞት ግን ዳዊትን ክፉኛ አሳዝኖት ነበር (2ሳሙ. 1) ሳኦል ደሙን ባዘራበት ተራራ ዳዊት ደግሞ እንባውን ረጨበት። እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም፥ የሳኦልን ሞት ተከትሎ፥ ዳዊት የእስራኤልን ዙፋን ወሰደ፤ በተለይም የይሁዳ ሰዎች የዳዊትን መመረጥ ተቀብለው አስቀድመው አነገሡት (2ሳሙ. 24)

 

ይኹን እንጂ፥ ይህ የሽግግር ጊዜ በጣም አስከፊ ኹኔታን መፍጠሩ አልቀረም። የዳዊትን መንገሥ ያልተቀበለው የሳኦል አጎትና የጦር ኀይሎቹ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበረው አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን አንግሦ ከዳዊት ቤት ጋር የጠብ ፍጥጫ ለመፍጠር ሞከረ። ዳዊት ለዚህ ጕዳይ የኀይል አማራጭ ለመውሰድ ማሰቡን የሚያመለክት ቀጥተኛ ፍንጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ምክንያቱም ለሰባት ዓመታት ያህል ግዛተ መንግሥቱን አጥብቦና መቀመጫውን በኬብሮን አድርጎ በይሁዳ ቤት ላይ ብቻ ንግሥናውን በማደላደል እንደ ቈየ አንብበናል።

 

አንድ ቀን ታዲያ እንዲህ ኾነ። የዳዊት ሠራዊት አለቆች መሪ የነበረው ኢዮአብና የኢያቡስቴ ጦር አለቃ አበኔር ከነጭፍሮቻቸው በገባዖን ውሃ መቆሚያ አጠገብ (2ሳሙ. 213) ተገናኝተው ማዶ ለማዶ ተፋጠጥው ተሰለፉ። ወንድሞች በኹለት ጐራ ቆመው ነበር። በዚህ ጊዜ፥ ለዓመታት የዘለቀውን መቃቃር በኀይል ለመቋጨት ይመስላል፥ አበኔር የይዋጣልን ሐሳብ አቀረበ። ከኹለቱም ወገን ደርዘን፥ ደርዘን የጦር ብላቴኖች መርጠን እናደባድብ በማለት የወንድሞች ጦርነት ለማስጀመር ቈርጦ ተነሣ። ኢዮአብም በሐሳቡ ተስማማ። አበኔርም ኢዮአብን፦ ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቈራቈሱ አለው፤ ኢዮአብም፦ ይነሡ አለ (2ሳሙ. 214) ከኹለቱም ወገን ዐሥራ ኹለት፥ ዐሥራ ኹለት ሰዎችተቈጥረው ተነሡ

 

ከዚህ በኋላ የኾነውን ነገር ለመግለጽ አሳዛኝ የሚለው ቃል በቂ አይመስልም።ኹሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፤ ሰይፉንም በወደረኛው ጐን ሻጠ፤ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በገባዖን ነው (2ሳሙ. 215) ወንድም ወንድሙን እንደ ያዘ ጥሎ-ወደቀ። እያንዳንዱ፥ በወንድሙ ላይ ሰይፉን ሽጦና ከወንድሙ በተሠነዘረበት ሰይፍ ላይ ተሽጦ፥ ገድሎ-ሞተ። የወንድም ሰይፍ የወንድምን ሕይወት በላ።ተያይዘውም ወደቁ፤ይልሃል መጽሐፍ።

 

ከዚያ በኋላ የኾነውን ምኑን እነግርሃለሁ። ቀሪው ጦር በየወገኑ ተከፍሎ እርስ በርስ ይከታከት ጀመር። አበኔርን ገድሎ ጀብዱ ለመሥራት የቈረጠ የሚመስለው የኢዮአብ ወንድም አሣሄል ጭምር በሰይፍ ተወግቶ እንደ ቦረቀ፥ ወደቀ። ከኢዮአብ ወገን (የእናቱን ልጅ ወንድሙን ጨምሮ) ኻያ ሰዎች፥ በአበኔር በኩል ደግሞ ሦስት መቶ ስድሳ ጐልማሶች ወድቀውናጐድለውመሸ፤ እስራኤል ሲጥልና ሲወድቅ፥ ፀሓይ ጠለቀች (. 24) ወንድም በወንድሙ ላይ የሰይፍ ስለት መዝዞ እየመታ አጕድሎ፥ ጐደለ።

 

በማለዳ ጠቡን ያስጀመረው አበኔር አመሻሽ ላይ ጦርነቱን ያስቈመበት መንገድ የሚደንቅ ነበር። በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመው፥ አየሩ በደም ሽታ እየታጠነ በነበረበት የጠብ ክርፋት መኻል አይቀሬውን ጩኸት ለማሰማት ተገደደ።አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ፦ ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ኾነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው(. 26) ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብ ጦርነቱን አስቈመ። በአጕል ጀብደኝነት ቀጥሎ ቢኾን ጥፋቱ ከተጻፈውም በከፋ ነበር።

 

እኛስ? የጠብና ሁከት መራራነት እስኪገባን ድረስ መቈራቈስ አለብን ወይ? “ይዋጣልንዐይነት ድንፋታ ማንን ይጠቅማል? ይህ እኮ፥ ማን ያሸንፋል በማለት የምንቀልድበት የልጆች ውሽንብር (ቍጥቻ፥ ውርርድ) አይደለም። አፋፍ ላይ ቆመን የምናንቋርረውወደ ፊት በሉለትዐይነት ቀረርቶ የሚቀሰቅሰውን እሳት እንዴትና መቼ ልናስቆመው አስበን ነው እንዲህ ከግራና ከቀኝ የተፋጠጡትን ወገኖች ዝም ብለን የምንሰማቸው? የሐሳብ ልዩነቶች ወደ ግጭትና ፍጅት እንዳያመሩ መደረግ አለባቸው። ወንድሞች ተያይዘው ከመውደቃቸው በፊትአሳርፍባይ ሽማግሌዎች እንዲነሡልን መጸለይም መጐትጐትም ይገባናል።  (በነገራችን ላይ፥ ይህየሽማግሌ ያለህጩኸት የከረመና ጥቂት ያልኾኑ ወገኖች ሐሳብ እንጂ  የኔ ብቻ አይደለም።)

 

ሽማግሌዎችን ዐሰሳ

 

በጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት ከመፈለግ ጐን ለጐን በምድር ላይ እንድናደርገው የተሰጠንን ኀላፊነት ለመወጣት መታዘዝ አለብን። የቍጣ ትረካዎች ይለዝቡ፤ልክ እናስገባዋለንፎካሪዎች አደብ ይግዙ፤ ሰይፍ ወደ ሰገባው ይመለስ፤ ሰደፍ ወደ ድኾች ሰርን አይጣደፍ፤ ምላስም ይሰብሰብ፤ ሰው የመኾን ክብርና አስተዋይነት ይታይብን፤ ንግግራችን ደርዝ ይኑረው። ሽማግሌዎች ይነሡ።

 

ከቤት እስከ ጎረቤት፥ ከሰፈር እስከ አገር ጠብ አብራጅ ድምፅ አስፈልጎናል፤አንተም ተው፥ አንተም ርጋሲል የሚደመጥ አባት አልናፈቃችሁም? በዛሬ ጊዜ ዕርቀ ሰላም በትኛውም ቦታ የሚያስፈልግ ነው። ጠብ ኅብረትን ያናጋል፤ ሰላምን ያደፈርሳል፤ ሕይወትንም ያሳጣል። ወንድሜ ሰላም ዐጥቶ እኔ ሰላም ሊኖረኝ አይችልም። ነገሩበጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል?’ እንደ ተባለው ኾኗል። ሲናገር የሚደመጥ አባት ያስፈልጋል። የሚኾነውን ስናይና ስንሰማ፥ የኾነ የሚያስቈዝም ነገር አንጃቦብናልና፥ እንዲህ ስንል እንጠይቃለን፤ ሽማግሌ የለንም ወይ?

 

እንዲህም ብለን እንብሰለሰላለን። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያችን ምንድር ናት? ሽማግሌ የሌላት አገር? … ወይስ ሽማግሌዎቿን በልታ የጨረሰች አገር?... ወይስ ሽማግሌዎቿ የማይደመጡባት አገር? … ወይስ ሽማግሌዎቿ በአርምሞ ያደፈጡባት አገር? እነሆ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ይህ ሐሳብ መንፈሴን እያልመዘመዘው አለሁ። አገሬ ሽማግሌዎች የሌሉባት (ያጣች) ወይስ የሌሉላት (ኖረውም እንኳ በሽምግልና ክብርና ሞገስ ያልተገኙላት) ናት? ምነዋ፥ ሽማግሌዎቻችንን የበላ ጅብ አልጮኽ አለሳ!

 

በዘመናዊው ዓለም መንግሥታዊ መዋቅሮችና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሊያከናውኑት የተገባውን ነገርሽማግሌ ምን ቤት ኾኖ ነው ጥልቅ የሚልበት?” የሚለኝ ሰው ይኖራል። ምላሹ እኒህ ተቋማት የአቅም ውሱንነት ከታየባቸው ሌላ ምን ይደረጋል? የሚል ነው። ወይም ኖረውም ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ካልቻሉስ? ወይም ተቋማቱ፥ እንደ እኛ ገና ድክ ድክ በማለት ላይ ባለ አገር እንደመኖራቸው፥ ድጋፍ ካስፈለጋቸውስ? ወይም እነርሱም በአስተዳደራዊ ጕድለት ከተጠቁስ? … ሽማግሌማ ያስፈልገናል።

 

በጥንታዊ ማኅበረ ሰቦች ዘንድ ሽማግሌዎች ይጫወቱት የነበረው ሚና ትልቅ ነበር። ዛሬም ቢኾን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት፥ በተለይ በገጠር ቀመስ አካባቢዎች፥ ኹለት ፀጕር ያወጡ አባቶች፥ የሃይማኖት መሪዎችና የየጐሣ አለቆች፥ እንደ ቀድሞው ዘመን ባይኾንም እንኳ፥ ይከበራሉ፤ ይደመጡማል። ስለዚህም በገጠመን ዙሪያ መለስ ምስቅልቅል ውስጥ እነዚህ አባቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ቀላል አለመኾኑን እያሰላሰልሁየሽማግሌ ያለህ!” ለማለት እገደዳለሁ።

 

ይኹን እንጂ እውነትን ጥሎ ሽበት ያበቀለ፥ ለኅሊናው ሳይገዛ ጺሙን ያንዠረገገ፥ ጽድቅን ሰባብሮ ከዘራውን የተመረኰዘ፥ ፈሪኀ እግዚአብሔርን አምዘግዝጎ ጥሎ የየሃይማኖቱን ካባ የለበሰ አዛውንት ይነሣልን ማለቴ አይደለም። ወገኑን የሚወድና ዕርቀ ሰላም የሚያወርድ ተክለ ሰብእና የተላበሰ ሽማግሌ ነው የናፈቀኝ።የናፈቀንእንዳልል፥ራስህን ቻልየሚለኝ ቢኖርስ ብዬ ነው። ሐሳቡን የሚጋሩ ብዙዎች ስለ መኖራቸው ግን ጥርጥር የለኝም። ለማንኛውም፥ መንፈሳዊ ልዕልናው ከአካላዊና ሥልጣናዊ ግዝፈቱ የጐላ ጎምቱ የፍቅር ሰው በዚች ትልቅ አገር፥ ምናለ በነበር!

 

ርግጥ ነው፤ ችግር ፈጣሪው ሰው ራሱ መፍትሔ አፈላላጊ ለመኾን ሲንጠራራ የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች በሽማግሌዎች ተስፋ ቈርጠዋል። እኔም ከአገራዊም፥ ማኅበረ-ፖለቲካዊም ኾነ ሃይማኖታዊ ችግሮቻችን መካከል ጥቂት የማይባሉቱ የተፈጠሩት በአዛውንቶች መኾኑን አላጣሁትም። ትውልድ ለመመረቅእንትፍ እንትፍሊሉ የተገባቸው የማኅበረ ሰብ አለቆች ትውልድ እንዲተራረድ ቂምና ጥላቻ ሲተፉ አይተናልና። ስለዚህም ነው ሽምግልናን የሚያሳብቁ ውጫዊ ገጽታዎች ባለቤት ከመኾን በላይ ልባዊ አዘንብሎት ላይ ማተኰር አለብን የምለው።

 

ሽማግሌ ይምጣልን ስል ያረጀ ያፈጀ አዛውንትን ብቻ በመከጀል አይደለም። የልብ ቅንነቱን በዘመን ክፋት ለውሶ ያላሳደፈ ሽማግሌ ነው የምመኘው።ምራቃቸውን የዋጡደጋግ ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል፤ እኒህ ተፈላጊዎች ታዲያምራቃቸውን በዋጡጊዜ እውነትን ተጕመጥሙጠው በአደባባይ ያልተፏት መኾን አለባቸው። ከስሕተታችንና ስሕተታችን ከወለደው መዘዝ ጋር ፊት ለፊት እንድንጋፈጥ በፍቅር የሚያግዙን ልበ-ሰፊ የአገር ባላዎች ወደ የት ይገኛሉ? ሽማግሌ ይፈለግ!

 

የቅን መንፈስ ባለቤት የኾነ፥ ነገአችን እንዳይጨላልም አሻግሮ የሚያይ ባለ ብሩህ ልቡና ሰው አስፈልጎናል፤ በመንፈስ ልዕልና የገዘፈ፥ ምክረ ልቡናው በሆይ ሆይታ ያልተዛነፈ  አባት፥ኅሊናው ላይ በሆዱ ያልተኛና ለነፍሱ ያደረ አረጋዊ፥አገር ሚዛን እንዳይስት የምግባር ክብደቱ ሞገስ ያላሳጣው ሽማግሌ ተመኘሁ ያው ምኞት መኾኑ ነው እንግዲህ። ምኞት በሕግም በጕልበትም ስላልታገደ መመኘቴን እቀጥላለሁ። የሽማግሌ ያለህ!

 

ከትናንት ጋር በብሶት መንፈስ ያልተጣመደ፤ ከዛሬ ጋር በክፋት አፍላል ውስጥ ያልተጣደ፤ ከነገ ጋርእኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀልበሚል ኪዳን ያልተጣበቀ፤ሽማግሌ፥ ክቡር አባት ፈለግሁ።የእብድ ገላጋይሰፈሩን እንዳይወርሽማግሌያስፈልገናል። የጠብ ቡድን አባቶች በርክተው በመንደርቶ መጣለዝ እንዳይስፋፋ አስታራቂ ገላጋይ ይነሣ። አስታራቂ ያጡ የአንድ እናት ልጆች የጋራ ጎጇቸውን አጋይተውለትኋኔ በጀኝብለው እንዳይጃጃሉ ሸምጋዮች ይገለጡ። ሸምጋዮች ይምጡ ስል የብቻዬ ሐሳብ ኾኖ አይደለም። የአስታራቂ ፍለጋው ጥረት የከረመ መሰለኝ። በዓሉ ግርማ፥ ያኔ ገና፥ በኦሮማይ፥ ይኸን የአስታራቂ መጥፋት እያሰበ እንዲህ እየቈዘመ ጽፏል፤ የአስመራ ጎዳና ዘንባባዎች ያረገዱበት መዝሙር አስመስሎ ነው በመጽሐፉ በኩል የሚነግረን። [4]

 

ያንድ እናት ልጆች 
በዓላማ ተለያይተው፥
በአመለካከት ተሳስተው፥ ተጣልተው፤
የሚያስታርቅ ጠፍቶ ፥

የዕብድ ገላጋይ በዝቶ። …

በዚያን ዘመን የሚያስታርቅ በመጥፋቱ ምን እንደ ተፈጠረ አሳምረን እናውቃለን። የአካልና የሕይወት ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ማኅበራዊ ውጥንቅጥ አስከትሎብናል፤ የታሪክ መዛበር ወልዶ ኼዷል፤ ሥነ ልቡናዊ መዳሸቅ አስከትሎ ነጕዷል። መዘዙ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ ይከተለናል። ለመነጋገር፥ ለመወያየትና ቅሬታን በምሕረትና ይቅርታ ለማስወገድ የማይችል ማኅበረ ሰብ የሚገባበትን ውጥንቅጥ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ኹሉ እኛም አይተነዋል፤ ቀምሰነዋልም።

 

ምንም እንኳ ይቅርታ መቀባበልና የእርቀ ሰላም ተግባር በአገራችን የተከበረ ዕሴት የነበረ ቢኾንም የእርቅ አቅምና ሥራ ግን መዳበር የሚገባውን ያህል ባለመዳበሩ፥በየሠፈሩ የሚከሠቱ ችግሮች ከመፍታት ዐልፎ አገራዊና ብሔራዊ ጕዳዮችን የማየት አቅም አላገኘም፤ በተለይ ሁሌም የችግሮች ኹሉ ቋት ኾኖ የቈየው የአገራችን ፖለቲካ እስካኹን ድረስ በአገር-በቀል ማኅበራዊ ዕሴትና ተቋም የመዳኘት ፍላጎት አላሳየም። ይህ ለችግሮቻችን መግዘፍና መወሳሰብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።” [5]

 

የአደባባይ ማነብነብ የጊዜው ፋሽን በኾነበት በዚህ ዘመን የሰከነና በሳል ውይይት ያስፈልገናል። ይህን መንገድ የሚያሳዩ አሰላሳዮችና ብሔራዊ አጀንዳ የሚቀርጹ ሰዎችም ወደ አደባባዩ መምጣትም ይኖርባቸዋል። እነርሱስ ቢኾኑ እስከሚጠሩ ድረስ መጠበቅስ አለባቸው እንዴ? አገራችን ትልቅ ናት፤ ችግሯም ውስብስብ ነው። የኹሉንም ትብብርና ጥረት ትሻለች።

 

በአገረ መንግሥታት ግንባታ ኺደት ውስጥ ሥፍር ቍጥር የሌለው ውጣ ውረድ መታየቱና መታለፉ የግድ ነው። ሚሊዮኖች በሚኖሩበት አገር፥ ብዙ ፍላጎቶች ባሉበት ምድር፥ ከምንገምተው በላይ የተወሳሰቡ ባህላዊ፥ ማኅበራዊ፥ ታሪካዊ፥ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች በተሸመኑበት ማኅበረ ሰብ መካከል የሰከነ እና የሠለጠነ ውይይት ያስፈልጋል። መደማመጥም ይጠይቃል። 

 

እንደ ተባለው፥ አገራዊ አስተዳደር ውስብስብ መኾኑ ግልጽ ነው። የሚፈታውም በመነቃቀፍ አይደለም። የቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የነበሩት ጀነራል ዐቢይ አበበ እንዳሉት፥

 

የአገር አስተዳደር የተወሳሰበ ፈትል ነው። በተለይም ብዙ ልማድና ብዙ ዐይነት ባህል ብዙ ዐይነትም ሥሪትና ብዙ ዐይነት ጠባይ ባለው ሕዝብ ላይ ሲኾን፥ የባሰ ውስብስብ ያለ [ልቃቂት] ነው። ይህንም ለመፍታት ችግሩ [የጋራ እንደ መኾኑ] መፍትሔውም የጋራ መኾን [ነበረበት። ኾኖም] አንዱ ሲቸገር ሌላው ለመርዳት አይሞክርም፤ አንዱ ሲነቅፍ የሚነቅፍበትን ነገር ሳይረዳው ተነቃፊውም ምክንያቱን ሳያቀው መነቃቀፍ ብቻ የሥራና የመሻሻል መዝጊያ ኾኖ ቀርቷል።  መነቃቀፍ አርቆ ማስተዋል የሌለበት የአለ ይበሉኝና የወሬ ማዳነቂያ መደብር ኾኖ ከመገኘቱ በስተቀር ፍሬ አፍርቶ አልታየም። [6] 

 

እንግዲያስአርቆ ማስተዋልያልጠፋባቸው የትውልድ ባለ አደራዎች ለምድሪቱ ያስፈልጓታል። ሰላም በሌለበት ልማት የለም። መተማመን በጠፋበት ዕድገት አይታሰብም። ቅንነት በማይገኝበት መረጋጋት ብርቅ ይኾናል። መረጋጋት ያጣ ሕዝብና መንግሥት ካለበት ፈቀቅ ማለት ይቸግረዋል።[7] ተኝቶ እንትፍ ማለት ዞሮ ዞሮ የሚጐዳው ራስን ነው።

  

አንድ የከፋ ነገር በአገሪቱ ላይ ከመድረሱ በፊት የሚደረግ መተባበርና መመካከር ብቻ ነው ከምንሠጋው ጥፋት ሊመልሰን የሚችለው። ከምንፈራው ነገር ማግሥት በጸጸት አለንጋ እየተገረፍን ከስሕተት ለመማር ለሚሞከርበት ፍርጃ ከመዳረጋችን አስቀድመን መጪውን አደጋ ለመከላከል መሞከር ብልኅነት ነው። አርቀው ማየት የሚችሉ ባለ ራእዮች ትውልድን ከመጪ መርገምት መከለል ይችላሉ። የፈሩት ደርሶበአንድ ዐይን ከማልቀስናከጸጸት ለመዳን መሥራት የሚገባው ዛሬ እንጂ ለከርሞ አይደለም። 

 

ልዩነትን ማቻቻል ካላወቅንበት ውጤቱ መራራ ይኾናል። ምሳሌ ለመምዘዝም ሩቅ መኼድ አይኖርብንም። የቅርብ አብነት አለን። ከታሪካችን የትናንት አገዳ አንዱ አንጓ በኾነው ትውልድዘመን የኾነውንና የታሰበውን በትዝብትና በቍጭት የሚዘክሩ በርካታ ሰነዶች በጕዳዩና በዘመኑ ተዋንያን ታትመው ወጥተዋል። ከነዚህ መካከል በክፍሉ ታደሰ ከተጻፉት ባለ ሦስት ቅጽ የዘመኑ ማስታወሻዎች መካከል በአንደኛው ውስጥ ደራሲው እንዲህ ሲል ይቈዝማል።

 

ተቃውሞው፥ ልዩነትን የማቻቻል ባህል በመጥፋቱ የተነሣ ሲኾን፥ በኋላ እንደሚታየውም፥ የኢትዮጵያ የግራ ኀይል አንዱ ባሕርይ ኾኗል። ልዩነትን ማቻቻል ባለሞኖሩ፥ ስድብ ቍጣ-አዘል ውይይቶች፥ አንዳንዴም ድብድብና ስም ማጥፋት የተለመዱ ክዋኔዎች ነበሩ።የግራው ርዕዮት እየተስፋፋ ሲኼድ ቡድነኝነትም ዐብሮ አደገ። የተለየ ሐሳብ የነበራቸውን እንደ ጠላትና ከኻዲ በመቍጠር የተለያዩ ስሞች ተሰጧቸው። [8]

 

እንግዲህ፥የግራ ኀይሎችውጥንቅጥና ዳፋው አገሪቱን እንዲሁ ግራ እንዳጋባ ይቀጥላል ወይስ ዕልባት የሚያገኝበት መንገድ አለው? ለመወያየት፥ ለመነጋገር፥ ለመደማመጥ እና እርቀ ሰላም ለማውረድ ያለመፈለግ ዝንባሌ በተከታታይ በመጡት ትውልዶች ላይ አልተጋባም ማለት ይቻላል?  ይኸን ለታሪክ፥ ማኅበረ ሰብና ፖለቲካ ምሁራን ጥናት እንተወው። ኹላችንም ስለ ጕዳዩ ማውጠንጠናችን ግን ይቀጥላል።

 

ብፁዓን ገባርያነ ሰላም

 

እስካኹን ያልሁትን ኹሉ ግን ለምን እላለሁ? ለእኛ ክርስቲያን ነን ለምንል ኹሉ ሰማይ የሰጠን ተልእኮ ነውና፥ እላለሁ። ታላቁ ጌታና መምህር፥ የሚያስተራርቁ [ዕርቀ ሰላም የሚያወርዱ] ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና (ማቴ 59 ቅንፍ የእኔ) እንዳለው የሚመላለሱና የሚኖሩ ቅን ሽማግሌዎች ወደ የት አሉ?

 

አንድ ማኅበረ ሰብ በእንዲህ ዐይነት ቅያሜ ላይ በደረሰ ወቅት ክርስቲያኖች እንደብርሃንነታቸው” (ማቴ. 514 ኤፌ. 58) በጨለማው ላይ ወገግታን ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። የእነርሱ ጥበብ ላይኛይቱ ናትና ለምሕረትና እርቅ ገርና ታዛዦች የመኾን ጥሪ አለባቸው። ሐዋርያው ያዕቆብ እንዳስገነዘበው፥ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል(ያዕ. 3 17-18) ሰላም አውራጅ ምእመናን የሰላም ልጆች ናቸው፤ የጽድቅ ፍሬ ይዘራላቸዋል።

 

የአንድ ማኅበረ ሰብ ምግባራዊ ዕሴቶች ጠውልገው በክፋት ዐውሎ ነፋስ እየተጠረጉ መወሰዳቸው የሚገታው እንዴት ነው? በወንጌል እውነት በተለወጡ እውነተኛ ምእመናን መነሣት ነው። ማኅበራዊ እብደት ነግሦ ሰብአዊ ፍጡራን በአውሬያዊ ደመ ነፍስ በሚካለቡ ጊዜ ከጥፋት ሊገታቸው የሚችል የጽድቅ ብርሃን ካላገኙ ማክተሚያው በጨለማ ግርማ መከደን ብቻ ነው። አገራችንም ወደ ከፋ ችግር ገብታ እንዳትዝረከረክ መፍትሔ የሚያፈላልጉ ብልኀተኞች መገኘት አለባቸው። / ደረጀ ከበደ በትንቢታዊ መልእክቱ እንደ ጮኸው፥

 

ማነው ነህምያ ቅጥሯን የሚጠግን?

ኀፍረተ ሥጋዋ እርቃኗ ሳይባክን። [9]

 

ዝማሬው እንጕርጕሮ አለው። ሐሳቡ ምጡቅ ነው። የደረጀ የምጡ ጥልቀት በግልጽ ይታያል። የምሕላው ክብደት ቀላል አይደለም። ከመስመሮቹ መካከል የሚታየው ምናባዊ ዓለም የአገር ፍንክት ነው። የሕዝብ ክብር ውርደት ነው። ከአፍላ ወጣትነቴ ጀምሮ በዚህ ምሕላ ያለማቋረጥ ድኼበታለሁ። ምጡ የአገር ምጥ ነዋ። የአገር ቅጥር መፈራረስ ተስፋፍቶ መዘዙ እንዳይከፋ ይማጸናል። ነገራችን ኹሉ መላቅጡ ጠፍቶ በአገር ሰማይ ላይ የጥፋት የሎስ እንዳያንጃብብ ይለምናል። የማኅበረ ሰብ ውልቃት እንዳይስፋፋ ስለ ወጌሻዎች መነሣት ይመኛል።

 

እንደው መላው ምንድር ነው? አንድም ወደ ልዑል አምላክ የሚቀርብ የልብ ጸሎትና ምሕላ ነው። የታሪክ ባለቤትና ጌታ የኾነው አምላክ ጸሎት ስለሚሰማ ምሕረትንም ማውረድ ስለሚቻለው ወደ እርሱ መጮኽን የሚተካ ሌላ መፍትሔ አይገኝም። ሌላው ደግሞ ከልብ በመነጨ የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ የሰላም መልእክተኛነትን መወጣት ነው። የሰላም መልእክተኛ ለመኾን ከእግዚአብሔርም ኾነ ከሰው ጋር ሰላም ያለን መኾን አለብን። ከእግዚአብሔር ጋር ሳትታረቅ ከራስህ ጋር እርቅ አታወርድም። ከራስህ ጋር ሰላምን ሳትፈጥርም ለሌሎች ሰላም አውራጅ አትኾንም። ልባችን የሰላም ዝማሬ የሞላው ከኾነ፥ ጸሎታችን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ የእርሱ መሣሪያ እንድንኾን መማጸንን ያካትታል። እርሱ እንዲጠቀምብን መለመን የትክክለኛ ክርስቲያን የልብ ዝንባሌ ነው።

 

ቅዱስ ፍራንሲስ ጸሎት ውስጥ እንዲህ የምትል ጣፋጭ ሐሳብ ትገኛለች፤ ጥላቻ በሞላበት ሥፍራ ፍቅርን እንድዘራ፥ የሰላም መሣሪያ አድርገኝትላለች። ሙሉውን ጸሎቱን ዐብረን ልንለው እንችላለን፤ ይኸው፥

 

ጌታ ሆይ፥

ጥላቻ በነገሠበት — ፍቅርን፥

ጕዳት በሚገኝበት — ይቅርታን፥

ተስፋ መቍረጥ በሠፈነበት — ተስፋን፥

ጨለማ በዋጠው ቦታ — ብርሃንን፥

ኀዘንና ልቅሶ በሞላበት — ደስታን እንዳዘምር

እባክህ የሰላም መሣሪያህ አድርገኝ።

 

አምላኬና ጌታዬ ሆይ፥

 

ሌሎችን ማጽናናት የሚገባኝን ያህል ለራሴ መጽናናት እንዳልሻ፥

ሌሎችን መረዳት ያለብኝን ያህል እኔን እንዲረዱኝ እንዳልጐመጅ፥

ሌሎችን መውደድ የሚኖርብኝን ያህል ለመወደድ እንዳልቋምጥ፥

ጸጋን ስጠኝ።

 

ምክንያቱም፥ የምንቀበለው በመስጠት፥

ይቅር የምንባለው፥ ይቅር በማለት፥

ለዘለዓለም ሕይወትም የምንወለደው በመሞት ነውና።

አሜን።

 

እንግዲህ የተወደዳችሁ ወገኖች ሆይ፥ተያይዘን እንዳንወድቅ ልባችን ለፍቅር ይውደቅ። ምሕረት አውራጅም ይምጣልን። እንዳንቈራቈስ፥ ሽማግሌ እናሥሥ። ምሕረትን ለማውረድ የተቈረሱ ልቦች ይስጠን። በመስጠት መቀበልን እንልመድ። ኹልጊዜ እኛ ብቻ የምናሸንፍበት ሳይኾን፥ አገርና ማኅበረ ሰብ የሚጠቀምበትን እናስበልጥ።

 

አንድ ዐይና በአፈር አይጫወትምየሚለውን ምክር አለመዘንጋት ለኹላችንም ይጠቅማል። ሞኛ ሞኝና ዕብሪተኛ መሪዎች እና ሕዝቦች ካከሸፏቸው ብዙ አገራት ውድቀት እንማር። ከጥቂት ግለ ሰቦችና ቡድኖች ጠባብ ግብ፥ ጊዜያዊ ጥቅምና፥ ዐንካሳ ድል በላይ አርቀንና ጠልቀን እናስብ። ለገላጋይ አሻፈረኝ ማለታችንን እናርቀው። ኢትዮጵያ ለኹላችንም የምትበቃ መሰለኝ።

 

አገሪቱን በሚመለከት እውነታው አይለወጥም፤ አገሪቱ በብዝኀነት የተሞላች ናት። የታላላቅ ታሪካዊ አሻራዎች፥ የተፈጥሮ ሀብቶች፥ ቅርሶችና ውርሶች ባለቤትም ነን። መልካም ነው። በታሪካችን ትልቅነትና በሌሎችም ነገሮች መመካት የለመደብን ሕዝብ መኾናችንንም አላጣሁትም። ከጐደሉን ነገሮች አንዱ ግን የመግባባቱ ጕዳይ ይመስለኛል። ምክንያቱም፥ ገጣሚው እንዳለው፥

 

“… ይህ [ጕደኛ ሕዝባችን] በልዩ ታሪኩ የኖረ፥
ገዳይ ተዋጊ ሳይኾን፥ ሽማግሌ ነው የተቸገረ።”
[10]

 

©ይህ ጽሑፍ በ2009 ዓ.ም. የተቈረሱ ነፍሶች በሚል ርእስ ከታተመው መጽሐፍ ላይ በደራሲው ፈቃድ ተወስዶ እዚህ የቀረበ ነው።

ማስታወሻ፦

ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን፥ የትሩፋን ናፍቆት (ዐዲስ አበባ፥2006 ..)183

2የዚህ ግጥም ደራሲ ማን እንደ ኾነ በትክክል ለማመልከት አልቻልሁም። የነቢይ መኰንን ነው የሚመስለኝ። ነገር ግን፥ እሱ ከኾነም የትኛው ሥራው ላይ እንደሚገኝ አላወቅሁም።

3 ጠና ደዎ፥ ሰው፥ ግብረ-ገብና ሥነ-ምግባር፦ የዘመናችን ቍልፍ ጕዳዮች  (ዐዲስ አበባ፦ ዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፥ 2008 ..) 484.

4 በዓሉ ግርማ፥ ኦሮማይ፥ 2 ዕትም (ዐዲስ አበባ፥ ኵራዝ አሳታሚ ድርጅት፥ 1984 ..) 27

5 ጠና፥ ሰው፥ ግብረገብና ሥነ-ምግባር፥ 484.

6 ዐቢይ አበበ፥ ዐውቀን እንታረም፥ 2 ዕትም (ዐዲስ አበባ፦ ቼምበር ማተሚያ ቤት፥ 1957 .)

32-33

7 ታዋቂው አሰላሳይ ነጋድረስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

8 ክፍሉ ታደሰ፥ ትውልድ፥  ቅጽ 1 3 ዕትም (ዐዲስ አበባ: በሱ ፈቃድ ታደሰ እና ኤሚ እንግዳ፥ 2007) 82-83 116

9 ደረጀ ከበደ፥ዐስባት እናት አገሬን፥ ብሩህ የድል ጠዋት፥ አልበም ቍጥር 8 1987 .ም።

10 አበባው መላኩ፥ሽማግሌ የሌላት ሀገርበከራዴዎን፥ (ዐዲስ አበባ፦ አሳታሚ አልተጠቀሰም) 79-80 (ከጥቂት የቃላት ለውጥ ጋር)

Read 8823 times Last modified on Thursday, 14 November 2019 08:13
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 169 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.