You are here: HomeSocial Issues የማን ልደት ነዉ?

የማን ልደት ነዉ?

Written by  Sunday, 25 December 2016 10:56

ሚሚዬ ልደቷ እየተቃረበ መምጣቱ ተደጋግሞ  ተነግሯታል። የዘንድሮዉ ለየት ባለ ሁኔታ በትልቅ ድግስ እንደሚከበርላት  ስለተነገራት ደስታዋ ወሰን አልነበረዉም። ወሬዋም አሳቧም እርሱዉ ሆኗል። ቤተሰብም ዝግጅቱን አጧጡፎታል።

 

እንዳይደርስ የለም ከብዙ ጥበቃ በኋላ ‘የሚሚዬ ልደት’ ቀን ደረሰ! በማለዳ የቀሰቀሳት የዝግጅቱ ግርግር ሲሆን ይህ ሁሉ ለእርሷ መሆኑ ገርሟት በደስታ ከአልጋዋ ዘልላ ወረደች።

 

እኩለ-ቀን ሲሆን ቤቱና ግቢዉ በታዳሚዉ ተሞላ። ፈንጠዝያዉ ቀጠለ፡- ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፈራል፣ ይሰከራል፣ ይሳቃል። በፈንጠዝያው መጨረሻ ግን ‘የሚሚዬ ልደት’ ማጠቃለያ ኬክ መቁረስ በመሆኑ አመሻሹ ላይ የልደቱ ኬክ  ሊቆረስ ተዘጋጀ።

  

ሆኖም ግን በዚህ ወሳኝ ጊዜ ሁሉንም ሰዉ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ተፈጠረ። ኬኩን ቆራሿ ሚሚዬ በአካባቢዉ ስትፈለግ ልትገኝ አልቻለችም። የሚያስገርመዉ ነገር በግርግሩ መሃል ባለልደቷ ለካ ተረስታ ነበር። ከጠዋት ጀምሮ ያስታወሳትም ያያትም ሰዉ አልነበረም። አሁን ግን ከመኝታ ቤቷ እስከሰፈር ድረስ ፍለጋዉ ቀጠለ።

 

ከብዙ ዉጣ ዉረድ ብሇላ ባለልደቷ ሚሚ ሰፈር ውስጥ ከሌሎች ልጆች ጋር እየተጫወተች ተገኘች። እንደዋና ባለጉዳይ ወግ ያለዉ ልብስ ያለበሳት እንኯ አልነበረም፤ የለበሰቻትም የሌሊት ልብስ አቧራ ለብሳለች። የሚሚዬ ወላጆች በቁጣ ተሞልተዉ “በልደትሽ ቀን አዋረድሽን!” የሚል የጩዀት ዝናብ ያወርዱባት ጀመር። ልጃቸዉ ያቀረበችዉን ብርቱ ጥያቄ ግን የሚመልሱበት የሞራል ብቃት አልነበራቸዉም።

 

የልጅ ዓይኖቿን ወደላይ እቅንታ እየተመለከተች፡- “እኔኮ ልደቱ የእኔ መስሎኝ ጠዋት በደስታ ነበር የነቃሁት። ትኩረት የሚሰጠኝና የሚያለብሰኝ ከማጣቴም በላይ የምታደርጉትን ሁሉ ዝም ብዬ ስመለከት ልደቱ የእናንተ መስሎኝ ነዉ ለመጫወት የወጣሁት። ለመሆኑ ልደቱ የማን ነዉ የእኔ ወይስ የእናንተ?” ለወላጆቿ ብቻ ሳይሆን በልጅ አመካኝተዉ ሲበሉ፣ ሲጠጡ ለዋሉ ‘አዋቂዎች’ ሁሉ ይቅርታ ከመጠየቅ  በቀር ሌላ መልስ መስጠት የቻለ አልነበረም።

 

ይህን አፈታሪክ ያነሳሁት ለምን እንደሆነ ሳይገባችሁ አልቀረም። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ደርሷል። በመሆኑም ገበያዉ ሞቅ ማለት ጀምሯል። የልደት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ ‘የኛ ብቻ’ እየሆነ መጥቷል። ከቤተክርስቲያናት ይልቅ ቤተመጠጦች የሚደምቁበት፤ የመብል የመጠጥ፣ የጭፈራና የሌሎችም ብዙ ’ራስ ማስደሰቻ’ ጊዜ አርገነዋል።

 

ባለልደቱ ተገልጦ “ለመሆኑ የማን ልደት ነዉ?” ቢለን መልስ መስጠት የምንችል ስንቶች እንሆን? የምናፍርስ?

 

ልደቱ የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ እርሱ የሚከብርበት ሊሆን ይገባል። “መድሐኒት ተወልዶልናል” (ሉቃ 2፡11) የሚል ብስራት የሚያስተጋባበትና “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ” የሚል  ዜማ ወደላይ ወደርሱ የሚያርግበት ሊሆን ይገባል።

 

በሉ ተነሱ ልደቱን እናክብር! ግን አስታዉሱ ልደቱ የኢየሱስ ነዉ! ክብርም ለእርሱ ነዉ! መልካም ልደት ይሁንልን!

Read 9211 times
Dr. Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Studied at

Website: mamushafenta.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 29 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.