You are here: HomeSocial Issues የደወሎቹ ድምጽ የተሰማበት ምሽት

የደወሎቹ ድምጽ የተሰማበት ምሽት

Written by  Thursday, 07 January 2016 17:56

“ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው፡፡” ምሳሌ 16፡16

 

በድሮ ዘመን በአንድ ወቅት፣ በአንዲት ታላቅ ከተማ ውስጥ ባለ ኮረብታ ላይ እጅግ ያማረ ቤተ ክርስቲያን ነበረ፡፡ በበዓላት ጊዜ በሕንፃው ውስጥ ያሉ መብራቶች ሁሉ ሲበሩ ከብዙ ማይል ርቀት ላይ ተሆኖ እንኳ ቤተ ክርስቲያኑን ለማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን፣ ይህ ቤተ ክርስቲያን ከውበቱ ባሻገር ሌላ እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ነበረው፡፡ እርሱም ስለ ደወሎቹ የሚነገረው እንግዳና አስገራሚ አፈ ታሪክ ነው፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኑ ጥግ አንድ ረዥም ማማ የነበረ ሲሆን፣ ሰዎች እንደሚናገሩት በማማው አናት ላይ በውበታቸው ከዓለም አንደኛ የሆኑ ደወሎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን፣ ለረዥም ዓመታት ማንም የደወሎቹን ድምጽ ሰምቶ አያውቅም፣ ለገና በዓል እንኳ ድምጻቸው ተሰምቶ አያውቅም፡፡ ያን ጊዜ በነበረው ልማድ መሠረት በገና ዋዜማ ሁሉም ሰዎች ለተወለደው ክርስቶስ የሚሆን ስጦታ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ያመጣሉ፡፡ አንድ ጊዜ፣ እጅግ የተለየ ስጦታ በመሰዊያው ላይ በተቀመጠ ጊዜ ከፍ ባለው ማማ ላይ ርቀው የተሰቀሉት ደወሎች እጅግ አስደናቂ ሙዚቃ አሰሙ፡፡ አንዳንዶች የደወሎቹ ሙዚቃ የተሰማው ንፋሱ አነቃንቋቸው እንደ ሆነ ሲናገሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ መላዕክት ደውለዋቸው እንደሆነ ገምተዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ግን ደወሎቹ ሙዚቃዊ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ የሚያበቃ ከፍ ያለ ስጦታ ቀርቦ አያውቅም፡፡

 

ከከተማይቱ ጥቂት ማይሎች በሚርቅ አነስተኛ መንደር ውስጥ ፔድሮ የሚባል ታዳጊ ወጣት እና ታናሽ ወንድሙ ይኖሩ ነበር፡፡ ስለ ደወሎቹ የሚያውቁት ነገር ባይኖርም በገና ዋዜማ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስለሚደረገው አገልግሎት ስለ ሰሙ የደመቀውን የበዓል አከባበር ለመታደም ወደዚያ ለማቅናት ወሰኑ፡፡

 

የዋዜማው ዕለት እጅግ ቅዝቃዜ የሰፈነበት ሲሆን፣ መሬቱም በተጋገረ በረዶ ተሸፍኗል፡፡ ምንም አጥንት የሚሰብር ብርድ ቢኖር፣ ፔድሮና ታናሽ ወንድሙ ከሰዓቱን መጓዛቸውን ጀምረው አመሻሹ ላይ ወደ ከተማዋ መግቢያ ደረሱ፡፡ ከትልልቆቹ በሮች በአንዱ ወደ ከተማይቱ ለመግባት ሲዘጋጁ በመንገዱ ዳርቻ አንድ ጠቆር ያለ ነገር አዩ፡፡

 

ጠጋ ብለው ሲያዩ መጠለያ ልታገኝ ወደምትችልበት ወደ ከተማው ውስጥ እንዳትገባ ሕመምና ድካም በበረዶው ላይ የጣላት ድሀ ሴት መሆኗን አወቁ፡፡ ፔድሮ ሊቀሰቅሳት ቢሞክርም ራሷን ስታለች፡፡

 

 

“ልቀሰቅሳት መሞከሬ ምንም እርባና የለውም ወንድሜ! ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ብቻህን መሄድ ይኖርብሀል፡፡”

 

“አንተን ጥዬ?!” አለ ታናሽ ወንድሙ፡፡

 

ፔድሮ በዝግታ ራሱን እየወዘወዘ “ይህቺ ሴት እንክብካቤ የሚያደርግላት ሰው ከሌለ በቅዝቃዜ ትሞታለች፡፡ ምናልባት በዚህ ሰዓት ሁሉም ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሄዶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከአገልግሎቱ በኋላ ስትመለስ የሚረዳት ሰው ይዘህ ተመለስ፡፡ እኔ እዚህ እቆይና ይብስ በረዶው እንዳይጎዳት ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ ምናልባት በኪሴ የያዝሁትን ዳቦ እንድትበላ ለማድረግ እችል ይሆናል፡፡”

 

“እኔ ግን ትቼህ አልሄድም” ሲል ታናሽ ወንድሙ ተከፍቶ ተናገረ፡፡

 

ፔድሮ “ሁለታችንም አገልግሎቱን ሳንካፈል መቅረት የለብንም፡፡ አንተ ሄደህ አንድ ጊዜ ለእኔ አንድ ጊዜ ደግሞ ለአንተ፣ ሁሉንም ነገር ሁለት ጊዜ መስማት እና ሁለት ጊዜ ማየት ይኖርብሃል፡፡ የተወለደው ክርስቶስ ምን ያህል ላመልከው እንደምፈልግ እንደሚያውቅ እርግጠኛ ነኝ! ደግሞ ይህቺን የብር ሽራፊ ውሰድና ማንም በማያይህ ጊዜ ስለ እኔ ስጦታ አድርገህ በመሰዊያው ላይ አኑርልኝ፡፡” ብሎ በመቅረቱ ዓይኖቹ ያቀረሩትን እንባ ለመዋጥ እየታገለ ወንድሙን አጣድፎ ወደ ከተማይቱ ላከው፡፡

 

ያን ምሽት ቤተ ክርስቲያኑ እጅግ ተውቦ ነበረ፡፡ ግድግዳዎቹ እስከሚርገበገቡ ድረስ በኦርጋኑ ድምጽ በመታጀብ ብዙ ሺህ ሰዎች ዘመሩ፡፡ በአገልግሎቱ ማብቂያ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ መሰዊያው እንዲያመጡ ጥሪ ቀረበ፡፡ አንዳንዶች ጌጦችን አንዳንዶች ደግሞ ክብደት ባላቸው የወርቅ ጥፍጥፎች የተሞሉ ቅርጫቶችን አመጡ፡፡ አንድ ስመ ጥር ጸሐፊ ለዓመታት ሲጽፈው የነበረውን መጽሐፍ አመጣ፡፡ ከሁሉም መጨረሻ ደግሞ የደውሎቹን ዝማሬ በሚሰጠው ስጦታ ለማሰማት እየተመኘ ንጉሡ ወደ መሰዊያው ቀረበ፡፡

 

ንጉሱ በከበሩ ማዕድናት የተንቆጠቆጠውን የንግስና ዘውዱን አውልቆ በመሰዊያው ላይ ባስቀመጠ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ በጉምጉምታ ተሞላ፡፡ ሁሉም ሰው “በእርግጠኛነት አሁን የደወሎቹን ድምጽ እንሰማለን!” አለ፡፡ ነገር ግን የተሰማው የቀዝቃዛው ንፋስ ጩኸት ብቻ ነበረ፡፡

 

የስጦታው ጊዜ ሲያበቃ ዘማሪዎቹ የመጨረሻ ዝማሬያቸውን ይዘምሩ ጀመር፡፡ በድንገት ኦርጋን የሚጫወተው ሰው መጫወቱን አቆመ፡፡ ዝማሬውም ቀስ እያለ ቆመ፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አንዲትም ትንፋሽ አልተሰማም፡፡ ሁሉም ሰዎች ለመስማት ጆሯቸውን አቁመው ሲጠባበቁ አነስተኛ መጠን ያለው ነገር ግን ከደወሎቹ የሚወጣ ድምጽ ተሰማ፡፡ ከብዙ ርቀት፣ ነገር ግን ጥርት ብሎ ከዚያ በፊት ከተሰማው ከየትኛውም ሙዚቃ ይልቅ ጣፋጭ ዜማ ፈለቀ፡፡

 

ሁሉም ሰው በአንድነት ብድግ ብሎ ለረዥም ጊዜ ዝም ብለው የቆዩትን ደወሎች ድምጽ እንዴት ያለው ታላቅ ስጦታ እንደ ቀሰቀሰ ለማየት ቆመ፡፡ ነገር ግን፣ ሊያዩ የቻሉት ማንም ሰው በማይመለከት ጊዜ ቀስ ብሎ ወደ መሰዊያው ሄዶ የፔድሮን ትንሽዬ የብር ሽራፊ ያስቀመጠውን ሕጻን ልጅ ብቻ ነበር፡፡

 

ከቺክን ሱፕ ፎር ዘ ክርስቲያን ሶውል ላይ ተመርጦ በሔርሜላ ሰለሞን የተመለሰ ወደ አማርኛ የተመለሰ

 

ሙሉ ማጣቀሻ:- Canfield, Jack, Mark Victor Hansen. Chicken Soup for the Christian Soul: 101 Stories to Open the Heart and Rekindle the Spirit. Health Communications Inc, 1997.

Read 6452 times
Hermela Solomon

Hermela Solomon is passionate about God and the Arts. She has written  continuous articles on Addis Admas, worked at Whiz Kids Workshop (tsehay memar twedalech) and contributed 3 books as part of the package to encourage Early Graders reading.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 141 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.