መሳካትን የማይፈልግ ማን አለ? ማንም የለም፡፡ የተሟላ ሕይወት ፍቺው እንደየተርጓሚው ቢለያይም የሰው ልጅ በጠቅላላው በእንጥልጥል ያለችውን ሕይወቱን አረጋግቶ ለማቆም ነው ደፋ ቀና የሚለው፡፡ የተመረጠ በልቶ ማደር ቢሆን ዐይን የገባውን ለብሶ መዋብ ቢሆን ከጎረቤት አንቱታ እስከ ሸንጎ ከበሬታ ሕይወት እንዲሳካለት የማይፈልግ ማነው? ይህ ሁሉ የሕይወትን ሙሉነት አያሳይም ቢባልስ? ሕይወት ተሳካች የምንለው ነፍስ በሰላም ስትረጋ ከአምላኳ ጋር ስትታረቅ ለሕዝብ ጠቃሚና ሁነኛ ሥራ ሲሠራ ነው የተባለስ እንደ ሆነ ይህም ቢሆን ያው የጎደለች ሕይወትን ሌላ ጠለቅ ያለ የምሉዕነት ገፅታ የሚመለከት ምኞት ነው፡፡
“ብፁዕ ብእሲ ዘኢ ሖረ በምክረ ረሲዓን …” ያለው ታላቅ ባለቅኔ ነበር፡፡ በመዝሙረ ዳዊት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚገኘው ይህ መዝሙር በአሉታ ብያኔ ጀምሮ ርእሰ ጉዳዩን እየፈታ የሚሄድ ቅኔ ነው፡፡ “የታደለው ሰው ብፁዕ ሰው፣ ምስጉን ሰው” ማን እንደ ሆነ በብርቱ ዘይቤ በዚህ አጭር ምዕራፍ ውስጥ ተነግሮአል፡፡ ይህ ምስጉን ሰው፡-
“በክፉዎች ምክር አይሄድም፤ በኀጢአተኞች
መንገድ አይቆምም፤ በዋዘኞች ወንበር አይቀመጥም”
የሕይወትን ሦስት ዋነኛ አውታሮች ማለትም የምንሰማው ምክር፣ የምንከተለውን መንገድ፣ የምናርፍበትን መንበር አጥርተን ልናውቅና ልንጠነቀቅ እንደሚያስፈልግ መዝሙረኛው አበክሮ ያሳስበናል፡፡ ሕይወት መቼ ነው የተበላሸው? የማይሆን ምክር ተከትለን የሄድን ዕለት፣ የተሳሳተ ጎዳና ላይ የቆምን ጊዜና መሠረት በሌለው ዋዛ ፈዛዛ ልቡናችንን ሞልተን የተደላደልን የመሰለን ቀን ነው፡፡
ይህ ሁኔታ አለመሳካትን፣ ጎደሎነትን፣ ብልሹነትን ያሳያል ብንል ከዚህ መቆጠብ ብቻውን ደግሞ የተሳካ ሕይወትን አያረጋግጥም፡፡ ከክፉ መታረም መልካም ቢሆንም ኅርመት ብቻውን መካን ፍልስፍና ይመስለኛል፡፡ የክርስትና ዋና ጥሪ ለመታረም፣ ለመከልከል ለመቆጠብ አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥሪያችን የማድረግ፣ የመግባት፣ የተሳትፎ ነው፡፡ ዳሩ ግን ወደ ተጠራንበት ግብ ስንሮጥ የሚያደናቅፈንን እንከላከላለን፤ እግራችንን ባደረሰው አንወረውረውም፤ እንታረማለን፡፡ የክርስትና የቅድስና አስተሳሰብ ሁለት መስተዋድዳን አሉት፤ “ከ” እና “ወደ”፡፡
ከክፉ የምንሸሸው ወደ መልካሙ ለመሮጥ ነው (2ጢሞ 2÷22)
ዘማሪው የአዎንታ ፍቺውን ይጀምራል “ዘዳእሙ ሕገ እግዚአብሔር ሥምረቱ” ዛሬ እኛ በተለይ ማወቅ ያለብን ይህ ብፁዕ ሰው ምን እንደማያደርግ ብቻ ሳይሆን ምን እንደሚያደርግም ነው፡፡ ምን ያደርጋል? “በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡”
የብፁዕ ሰው የተሳካ ሕይወት ምሥጢር እዚህ ላይ ነው፡፡ የደስታው ምንጭ የእግዚአብሔር ሕግ ነው የቃሉን ሕግ ሲያስብ አይጨፈግገውም ፊቱ ይበራል እንጂ፡፡ ተናጋሪውን ስንወድ ቃሉንም እንወዳለን፡፡ እናንተ ወዳጆቼ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለመስማት ጣር የበዛባችሁ እንደ ሆነ ራሳችሁን በዚህ ፈትሹ፡፡ ለመጽሐፉ ደራሲ ያለኝ ፍቅር ምን ያህል ነው አክብሮቴስ እንደምንድነው? በመዝሙር 37÷4 ላይ እንዲህ ይላል፤ “እግዚአብሔርን ተድላ አድርግ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” የምድር ዓለም ሁሉ ፈጣሪ የኛ አባት ምንም ትልቅ ቢሆን ከእውቀታችንም ሁሉ ቢመጥቅ ሊያስደስተን የሚችል አምላክ ነው፡፡ እርሱን ተድላ ስናደርግ ቃሉም ይጣፍጠናል፡፡ “ምስክርህ ተድላዬ ነው ሥርዐትህም መካሪዬ” ለማለት ድፍረት እናገኛለን፡፡ የዚህ ዘመን ሰው ደስታ በምን ላይ የተመሠረተ ነው? ክርስቲያኖች ነን የምንለው ራሳችንስ የቅዱስ ቃሉን እንጀራ እንዴት ጣፍጦን እንበላ ይሆን?
መዝሙራትን የጻፉት አባቶች የቀንና የሌሊት አሳብ የእግዚአብሔር ቃል ምክር ነበር፡፡ “በትእዛዝህ እጫወታለሁ” እንዳለው ዘማሪው ልቦናቸው በዚህ መጽሐፍ የተሞላ ነበር፡፡ ብጽዕናን ለሚለኩት ሰው ለእግዚአብሔር ቃል ባለው የሩቅ አክብሮት ብቻ ሳይሆን በዕለት ዕለት ሕይወቱ ውስጥ እውነቱ በሰረጸበት መጠን ነበር፡፡ ቃሉ ለላንትካ፣ ለታይታ መደርደሪያ ላይ የተቀመጠ ዕቃ ሳይሆን ለዕለት ርምጃ ምክር የሚጠየቅ ካርታና የሕይወት ፋና ነበር፤ “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም በርሃን ነው” ብሎ እንዳለው፡፡ የኑሮ ዜማችን በጠቅላላው የተቃኘው በዚህ መጽሐፍ እውነት እንዲሆን ነው ጥሪው፡፡
ይህ ቃለ እግዚአብሔር አንባቢ ቃለ እግዚአብሔር ኗሪ ሰው የቡሩክነቱን ውጤት ሲጀምር ባለቅኔው እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከትለች ዛፍ ይሆናል፡፡››
የመጽሐፉን እውነት እየጠጣ የሚያድግ በጎ ተክል የማያቋርጥ የሕይወት ምንጭ አጠገብ ተተክሏልና መልካም ውጤት ቢያስከትል አይገርመንም፤ ሦስት የሚያስደስቱ ሐረጎች ተጠቅሰውለታል፡፡ በዚህ ዘይቤ፡-
ፍሬውን በየጊዜው የሚሰጥ፣
ቅጠሉ የማይረግፍ፣
የሚሠራው ሁሉ የሚከናወንለት
ፍሬ የአንድ አፍታ ሥራ አይደለምና ነው በየጊዜው የተባለው፡፡ ቃሉን የሚያሰላስል ከነፍሱም ጋር የሚያዋህደው ሰው ይዋል ይደር እንጂ በተገቢው ሰዓት ጣፋጭ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም፡፡ የምዕመናንን ሕይወት በዝግታ ከመልካሙ የእግዚአብሔር ቃል ምንጭ ከማጠጣት የቤተክርስቲያን መሪዎች መቆጠብ እንደማኖርባቸው መዝሙረኛው ይጠቁማል፡፡
ፍሬ ጊዜ ይጠብቅ እንጂ ቅጠሉ የሁልጊዜ ነው፤ አይረግፍም፡፡ የሕይወት ምልክት ሁልጊዜ ይታይበታል ይህ ሰው ማን ነው? ቃሉን በቀንና በሌሊት የሚያስበውና የሚኖርበት፡፡
የሁላችን ምኞት የሆነውን ክንውንን ወይም መሳካትን ይህ ሰው ያገኘዋል፡፡ በታላቁ መካሪ ጎዳና ሄዷልና ያሰበበት ይደርሳል፡፡ ግን እንዲያው ለነገሩ ይህ ሰው የሚሠራው ምንድን ነው የተባለ እንደ ሆነ መሳካቱን ከቃሉ እንደሚያገኝ ሁሉ ሥራውንም ከዚያው ቃል ያገኛል ብንል ያስኬዳል፡፡ ስለዚህ አምላክን የሚያስደስት ነገር ያስባል፤ ያንኑ ይወጥንና ይሠራል፤ ክርስቲያን “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል ሰውስ ስለነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማር 8÷36-37) የተባለበትን መጽሐፍ ቅዱስ የምናምን መሳካት ማለት በእግዚአብሔር ዐይን ምን እንደ ሆነ ሳይገባን አይቀርም፡፡ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነው” (ፊል 1÷21) የሚለን ቅዱስ ጳውሎስ ተሳክቶለታል፡፡ ስለዚህ የመከናወንን ትክክለኛ ቃልም የምናገኘው ከዚሁ መጽሐፍ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብ ፈጽመን ማለፍ ጸጸት የሌለበት መከናወን ነው፡፡
“እኮ ከመዝ ኀጥአንስ አኮ ከመዝ”
ኀጥአንስ እንዲህ አይደሉም እነርሱ ሥር የላቸውም ታይተው ይጠፋሉ፡፡
ነፋስ ጠርጎ የሚወስደው ትቢያ ናቸው፡፡
በውሃ ፈሳሾች ዳር አልተተከሉምና የአንድ አፍታ ብቻ ጌጥ ቢሆኑ አይገርምም፡፡ በተመረመሩ ጊዜ ሊቆሙ አይችሉም፡፡ ያሁኑን ዓለም ምን ሞልቶታል የተባለ እንደ ሆነ ትቢያ ብቻ እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ አየሩ ሁሉ ለአፍታ በሚነሳ አቧራ ታፍኗል፡፡ ለአንድ ሰሞን በሚደምቅ ውልብልብታ ተጋርዷል፡፡ የሰዎች ነፍስ ረብ የሌለውን አመድ ይምጋል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ንጹሕ አየር እንድንተነፍስ ይርዳን፡፡ እኛም በቃሉ ተሞልተን ለብዙዎች የሕይወት ሽታ እንድንሆን ያብቃን፡፡