You are here: HomeOpinionsየመፅሃፍ ቅዱስ ባለ ሥልጣንነት እና ማእከልነት

የመፅሃፍ ቅዱስ ባለ ሥልጣንነት እና ማእከልነት

Tuesday, 19 December 2017 07:14

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ካሳደረበት ችሎታ ወይም አቅም መካከል ማስተዋለ ቃል አበጅቶ፣ ስም ሰይሞ ቋንቋ ቀምሮ መናገር ነው። በቋንቋ ዐሳብን መለዋወጥ መግባባትን ማራመድ ነው። እግዚአብሔርም በሰዎች ቋንቋ በሰዎች አማካይነት ዐሳቡን ለሰው አስተላልፏል፣ ቃሉን ሰጥቶናል፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፈውልናል። መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጕሞ ዛሬ ቀርቦልናል።

 

ቃሉ እውነታን ያሳየናል፤ እውነትን ያሳውቀናል፣ ማስተዋልን ያላብሰናል። መልካሙንና ክፉውን ይለይልናል፤ ስለ ፍጥረት፣ ስለ ፈጣሪ፣ ፈጣሪ ከፍጥረቱ ጋር ስላለው መስተጋብር፣ ስለ ስፍነ ተክል እና እንስሳ፣ ስለ ሰው አበጃጀት ወይም አፈጣጠር፣ ስለ ሰማይ ሠራዊት፣ ስለ መንፈሳዊ አካላት ይነግረናል፤ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ስላለው አምላካዊ ኪዳን ይተርክልናል። ሰው ከእግዚአብሔር ጋርና ሰው ከሰው ጋር ሊኖረው ስለሚገባ አኗኗር መመሪያ መመርመርያ ይሰጠናል። ስለ ውድቀት ያስረዳናል፣ ስለ ድነት መንገድ ይገልጥልናል፤ ስለ ዘላለም ሕይወትና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እውነታ ያወሳልናል መግቢያ መንገዱንም ያሳየናል።

 

ቅዱስ ቃሉ የእምነትና የአስተምህሮ መርሕ፣ የሞራል ሕይወት መለኪያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት መሠረት፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ምንነት፣ ዕውቀት መገብያ የትክክለኛና የጠራ አስተምህሮ ምንጭና ሚዛን፣ የፍትሐዊ አመራር ጥበብ መመንጫ፣ ለተሰጠ መሪነት ልብ መታነጫ እንዲሁም የሕያው እምነት መሠረትና መገንቢያ ነው።

 

እንግዲያስ ቃሉ

  • የነባራዊ እውነታ መሠረት፣
  • የእውነትና የሥርዐተ እምነታችን መገንቢያ
  • የሥርዐተ እሤታችን መዋቀሪያ
  • የልቡናችን መታደሻ፣ የአደራረጋችን፣ የአካሄዳችን፣ የአኗኗራችን መመሪያ ነው፤ በጥቅሉ የርዕዮተ ዓለማችን መታነጫ ነው።

 

ቃሉ እስትንፋሰ መለኮት ያደረበት በመሆኑ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰጡ ትእዛዛትን፣ መመሪያዎችንና መርሖዎችን የያዘ መጽሐፍ ነው። ስለሆነም ከወጋችን፣ ከልማዳችን ከዕሳቤዎቻችንና ከባህላችን ጋር ባይስማማም ፍጹም ሥልጣናዊነቱ አይሻርም።

 

መጽሐፍ ቅዱስ በቂ መገለጥ ነው፤ ይህም ማለት የእግዚአብሔር ቃል ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ፤ ለድነትና ለእርሱ ክብር ለመኖር የሚያስችል የተሟላ መልእክት ያለው ነው።

 

ባህል፣ የግል ልምምድ (ተሞክሮ) ስሜታዊ ማንነታችን፣ የወቅቱ ሁኔታ ሁሉ በጎም ክፉም ተጽእኖ ሊያሳድሩብን ቢችሉም እነዚህ ሁሉ ለቃሉ መገዛት ለሥልጣኑም ማደር ይኖርባቸዋል።

 

ነገሩ እንዲህ ሆኖ እያለ ግን ዛሬ በአብዛኛው ምእመናንና አገልጋዮች ዘንድ ያለው እምነት ከቃሉ ይልቅ በልምምድና በስሜታዊነት ላይ የተመሠረተ ሆኗል። በትምህርትም ሆነ በዕለታዊው ኑሮ ʻምን ታየህ?ʼ፣ ʻምን ተሰማህ?ʼ ማለት እጅግ ይበዛል፣ ይዘወተራል። ከእግዚአብሔር ቃል ዳኝነት ይልቅ ተሞክሮና ልምምድ የብዙኀንም ድምፅ ይገንናል። ለአስተምህሮ ትክክለኛነት ከተጨባጭና ከነባራዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ይልቅ ልምምዳዊ የሆኑ ማስረጃዎች ስፍራ ይሰጣቸዋል። ቃሉን ማሰብ፣ ማጤን፣ ማስተዋልን መጥላት፣ ገሸሽ ማድረግ ይታያል። ጸረ ተምህሮት (an -intellect) እና ጥራዝ ነጠቅ (quasi-intellect) የሆነ አቋም በእጅጉ እየተንጸባረቀ እውነትን ለማስተዋል የማሰብ ተግባር ቀስ በቀስ እየተኮላሸ፣ እንዲጨፈለቅ እየተደረገ ነው።

 

ዛሬ በሚያስደነግጥና በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ይህ የከበረው የአምላካችን ቃል የማይለውን ʻይላልʼ የሚለውን ʻአይልምʼ ብሎ ተርጒሞ ማስተማር እጅግ እየተበራከተ መጥቷል። አንዳንዶቻችን ግልጽ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይልቅ፣ ከቀጥተኛው ትምህርት (መልእክት) በስተ ጀርባ ፈለፈልን ብለን የምናወጣውን ትርጉም እናከብራለን። ከዐውዱ ጋር ወይም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተመርተው መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መልእክት ይዘት ጋር ባይጣጣምም አይገደንም። ይህ ያለንበት ጊዜ በሰዎች ምናባዊ ዓለም የተወለደ ትርጒም፣ ከእግዚአብሔር የመጣ መገለጥ እየተባለ የሚሰበክበት፣ አዳማጩም ʻአሜን አሜንʼ እያለ ያለ ምንም ፍተሻ፣ ያለ ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚዛን እንዲወስድ የሚደረግበት ጊዜ ሆኗል። ከዚህም የተነሣ ብዚዎቻችን የዘመኑ ሰባኪያንና አስተማሪዎች ራሳችንን ከመጽሐፍ ቅዱስና በመንፈስ ተመርተው ከጻፉት ነቢያትና ሐዋርያት በላይ በማድረጋችን ከእውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጋር ተጣልተናል፤ ለሐሰተኛ ትምህርት በሩን ወለል አድርገን አስከፍተናል።

 

ጊዜ ወስደን የእግዚአብሔርን ቃል ከማጥናት ይልቅ፣ ሁሉን ነገር መንፈስ ቅዱስ ይገልጥልኛል የሚለውን አባባል ለስንፍናችን መመከቻ እያደረግን ቃሉን ከፍተን ሳናነብ፣ ሳናጤን በመድረክ ላይ የምንቆም ብዙዎች አለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ አንድን ጥቅስ ወይም አንድን ምንባብ ዐውዱን ባላገናዘበ ሁኔታ ዘንጥለን በማውጣት፣ የራሳችንን ፍላጎት ሐሳብና አእምሯችን የወለደውን ትርጒም መደገፊያ፣ እንደ መዋኛ ስፍራ መወናጨፊያ ማማ አድርገን እንጠቀምበታለን። ያነበብነውን ክፍል ገልጦ ማብራራት ይቅርና ዳግመኛ ወደ ክፍሉ ሳንመለስ እንዳሻን ጋልበን እንደ ወጣን እንቀራለን።

 

ለዚህ ዐይነት ፈሩን ለለቀቀና የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጒም አዛብቶ ለመስበክና ለማስተማር የዳረገን አንደኛው ምክንያት ሰባኪዎችና አስተማሪዎች የሆንነው የመጽሐፍ ቅዱስን ምንነት በአግባቡ ረጋ ብለን ያለመረዳትና እንዴት አድርገን በትክክለኛው መንገድ መተርጐም እንዳለብን ያለማወቅ

 

ወይም ያለመፈለግ ነው። እግዚአብሔር የማዳን ታሪኩን የሰዎችን ባህልና ቋንቋም ተጠቅሞ ስለ ገለጠው መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የመልክዓ ምድራዊና ባህላዊ ዳራውን እንዲሁም ሥነ ጽሑፋዊ ዐውዱን፣ ሥነ ቃላቱንና ሰዋሰዉን ባስተዋለ ሁኔታ ልንተረጒመው ይገባል፤ የጽሑፉን ጾታና የአነጋገር ዘይቤውንም ልናጤን ያስፈልጋል። ዛሬ ብዙዎቻችንን የሥነ መለኮት ትምህርት ወይም የሥነ አፈታት ትምህርት ባንማርም፣ በቀላሉ የአስተውሎት ሕግ (common sense) ብቻ በቀጥተኛ ሁኔታ ሊተረጐሙ የሚችሉትን ክፍሎች እንኳ አዛብተን እንግዳ ትርጒም ስንሰጥ እንገኛለን።

 

በኤፌሶን 6 ላይ እንደ ተጻፈው የመንፈስ ሰይፍ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነውና ሁለቱን ማለትም መንፈሱንና ቃሉን ማፋታት የማይገባና ለስሕተት የሚዳርግ ነው። እኛን የሞላ/የሚሞላ መንፈስ ቅዱስ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈው/የደረሰው ያው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ዘወትር አበክረን ማስተዋል አለብን። ʻጌታ ተናገረኝ፣ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚያን ቀሳቅሰኝʼ እያልን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠን መመሪያ ውጭ ብንመላለስ ልምምዳችን በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል እንጂ ቃሉ አይወድቅም። ልምምዳችን ከመንፈስ ቅዱስ ከሆነ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይስማማል፤ አለበለዚያ ልምምዳችን ከራሳችን ስሜት ወይም ከክፉ አስመሳይ መንፈስ ወይም የሆነ ጥቅምን በመፈለግ ከሽንገላ ወይም ከአእምሮ ጤና ቀውስ ወይም ከዕውቀት ማነስ ሆኖ ይገኛል፤ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ራሱን አይቃረንምና።

 

“... እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ።” (2ጢሞ. 2፥15፡-)

 

“የመዳንን ራስ ቊር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ኤፌ. 6፥17)

 

የእውነት መንፈስ የሆነው፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራው መንፈስ ቅዱስ የቃሉ ደራሲ ነው። ስለሆነም ቃሉ የሕይወት፣ የእምነት፣ የአስተምህሮና የአምልኮ ማእከል መሆኑ በሁሉ ሁኔታ መረጋገጥ አለበት።

 

የተሐድሶ ጥሪ መመርመር - መመለስ - መታደስ በሚል ርዕስ ከቅረበው ጥናታዊ ፅሁፍ የተወሰደ።

Read 6160 times Last modified on Tuesday, 19 December 2017 08:30

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 65 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.