You are here: HomeOpinionsየአስተምህሮ ጥራት

የአስተምህሮ ጥራት

Monday, 16 October 2017 09:06

እውነተኛውን ወንጌል የሚሰብኩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ በታማኝነት የሚቆሙ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በሕይወትም፣ በትምህርታቸውም የሚያከብሩ አገልጋዮች መኖራቸው እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ምክንያት ነው። አሳሳቹን የዘመኑን ነፋስ እየተቋቋሙ እውነተኛይቱን መንገድ ለመጠበቅ የሚጥሩ ቅን ምእመናንም በየስፍራው አሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ በአጠቃላይ ሲታይ ግን የቀናና የጠራ ትምህርት እጦት እየተባባሰ መጥቷል።

 

የክርስቶስ ተከታዮች የተባልን እኛ ይብዛም ይነስም እንጂ በብዙ ረገድ ከመሥመር የወጣን፣ ከደረጃ የወረድን፣ አሳሳች ወለብላባ መልክ ያበጀን እንደ ሆነ ከገባን ቆይቷል። ይህ ብልሽት ሁለንተናችንን ያዳረሰ ቢሆንም የሚጀምረውና የሚጎለብተው በአስተሳሰብና በአስተምህሮ መደብ ላይ መሆኑ ብዙ የሚያነጋግር አይደለም።

 

ትምህርታችን ከተጣመመ የሕይወት ጉዟችን እንደሚሰነካከል ግልጽ ነው፤ ብልሹ ሕይወትም ተመልሶ አስተምህሮን ይበራራርዛል፤ አስተምህሮ ሲበረዝ ወይም ሲሸቃቀጥ ወይም ባዕድ አስተሳሰብ ሲጫነው ኑሯችን ውልግድግድ ይላል። ሕይወታችንንና አገልግሎታችንን በማነጽ ፈንታ የተገነባውን እየናደ እየፈረካከሰ ይሄዳል ወይም የማያለማ የማያሰማ ከጽድቅ የራቀ ፋይዳ ቢስ እየሆነ ይመጣል፤ አንድነታችን ይናጋል፤ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ስም ያሰድባል፤ ለክብሩ ወንጌል መስፋፋት እንቅፋት ይሆናል።

 

ባለፉት ሁለት ዐሥርት (ዓመታት) በእኛ በወንጌላውያን መካከል የተከሰተው የእውነት ቃል መንሸራተት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል:: በቤት፣ በቤተ ክርስቲያን ምስባክ፣ በመገናኛ ብዙኀን፣ ይህም ማለት በኅትመት፣ በኤሌክትሮኒክ መገናኛ፣ በኢንተርኔት፣ በስብከት ቃል፣ በትንቢት ቃል፣ በጸሎት አንደበት፣ በመዝሙር ቃል፣ የሚተላለፈው በየመስኩ ሁሉ ላይ የተዘራው፣ የበቀለውና የሚሰበሰበው መከር በርጋታ መበጠር፣ መፈተሽና መጤን አለበት።

 

ሜዳውን የሞላው እንክርዳድ፣ ʻየትከብራለህʼ ሰበካ፣ ሣርና ሥራ ሥር አብዛኛው ገዳይ መርዝ ነው፤ ያልገደለም እንደ ሆነ፣ ዐቅም እያሟሸሸ አጥመልምሎ ቤት የሚያውል ወይም ልቦናን እያነሆለለ የሚያስቀባዥር ክፉ ሥራይ (መርዝ) ነው።

 

መስኩን የሞሉት የግል ገድላ ገድል ትረካ፣ አልፎ አልፎ መስቀሉም ቢነሣ የክርስቶስን መስቀል ትሩፋቱን እንጂ አርአያውን፣ ማለትም መስቀል ተሸክሞ ጒዞን የማይዳስሱ ትምህርቶች ናቸው። ስሙን እያነሡ፣ ያስገኘልንን ጥቅም እየዘከሩ ነገር ግን መስቀሉ የሕይወት ዘይቤ የአካሄድ ፋና የሌለው ይመስል በረከቱን ዘርፎ የራሱን ሩጫ ሰው ሁሉ በየፊናው በመሰለው እንዲሮጥ የሚያበረታቱ አስተሳሰቦች ናቸው። ʻእርሱ መስቀሉን ተሸከመʼ እንልና ʻእኛ መስቀሉን እንሸከምʼ የሚለውን እንዘለዋለን፤ ʻእርሱ ስለ እኛ ሞተʼ እንልና ʻእንግዲያስ እኛም ሞትንʼ የሚለውን እንዘለዋለን:: መስቀሉ ማትረፊያ ብቻ እንጂ መኖሪያ መሆኑን አናወሳውም።

 

የእግዚአብሔርን መንግሥት አስቀድሞ ከመሻት ከመስበክ ይልቅ የእኛኑ መንግሥት ማስፋፋት፣ ያሁኑንና የዚህን ዕለታዊ ኑሮ ምቾት ምድራዊ ምኞትና ጥማት ለማሟላት ገንዘብ ንብረታዊ ብልጽግናን እንደ ባንዲራ እያውለበለብን ነን። ይሄው እንግዳ ዘር በየመስኩ ላይ በቅሎ እየተኮተኮተለትም ያለ ነው። በክርስቶስ ተከታዮች ልቦና ፍቅረ ንዋይን መዝራት፣ ሃይማኖትን የስግብግብነት ችግኝ ማፍያ መደብ ማድረግ እንዴት አያስጠይቀንም ትላላችሁ? ለጌታ አገልግሎት በራስ ፈቃድና በደስታ ገንዘብ የመስጠትን የልግስና ጥሪን በአጸፋው በሚገኝ አማላይ የደለበ ኪስ ተስፋ እንቁልልጩ እንዴት እንቀሰቅሳለን? የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ እያጡ ወንጌል በሰበኩት ቀዳሚዎቻችን ላይ የምንሳለቀውስ በምን ድፍረት ነው?

 

“ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” የሚለው ክቡር ዐዋጅ የፌዝ ቃል እስኪመስል ድረስ ያለ ውስጣዊ ልቡና ተገዥነት ይለፈፋል፤ የእርሱን ጌትነት ከእኛ ሎሌነት ለምን እናፋታዋለን? ይልቁን ይባስብለን በእርሱ ፈንታ ሰዎችን አጌተየን (አነገሥን)፣ ሥጋ ለባሾችን አደመቅን። በየስብከቱ የሚደመጠው የሥጋ ለባሽ ልዕልና፣ መለኮት አከል ግርማና የነገር ሁሉ ማእከል እስኪመስል ድረስ ማንቆለጳጰስ ምን ይባላል? ምንስ ጸጋ ቢሰጠው፣ ምንስ ችሎታ ቢኖረው፣ ምንስ የደለበ ልምድ ቢያካብት ሰው አምላክ የሆነ ይመስል በግለ ሰቡ ፊት ማደግደግና የዝና ማራገቢያ ይዞ ዙሪያውን መሽከርከር ማሸርገድስ ምን ይባላል?

 

በየተረተሩ፣ በየጉብታው አጀፍጅፎ የበቀለው ሸለቆውን ሁሉ የሞላው ነገር ደግሞ ሽለላን ፉከራን የተከናነበ ባዶ ጩኸት ነው። በውጫዊ ድምፅ ብርታት የሚያምን፣ በአምላኩ ፊት ጥሞናን ግን እጅግ የሚፈራ በጸጥታ የሚፈሰውን ሰማያዊ ኅብረ ዜማ ለመስማት የልብ ጆሮው ያልተቃኘ፣ የራሱን ድምፅ በመስማት ግን ጮቤ የሚረግጥ፣ የሚቦርቅ፣ የሁካታ እንቅስቃሴ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ አለ።

 

መጽሐፉ ʻቤቴ የጸሎት ቤት ይባላልʼ አለ፤ ʻየመንፈሱ ማደሪያ ለመሆን አብረን የምንሠራ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነንʼ ተባልን፤ ይህን ሁሉ እየሰማንና እኛም እያወራን ርግጡን ስንጠይቅ ግን ቤቱ በብዙ ቦታ የሸማችና የሻጭ የገበያ አዳራሽ መሆኑን መካድ አልቻልንም። እኛ አገልጋዮቹ ገበያ እንዳናጣ የማናጤሰው የጢስ ዐይነት የለም። ሸማችነት የተጠናወተው አማኝ ማኅበረ ሰብም እንደ ሱቅ በሚያያት ጸሎት ቤት አዳዲስ ዕቃ ካልገባ ጥሎ ለመሄድ አያመነታም። “ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርብ” ሙሽራው ዋጋ ከፍሎ ሳለ የእኛ ውሎ ግን በሌላ ሌላ ጉዳይ ላይ መሆኑ እጅግ እንግዳ ነገር ነው፤ ከክፉ ዱር ነፋስ ያመጣው ባዕድ ዘር ነው። ቅዱስ ደሙን አፍስሶ የገነባውን የቤቱን ባለቤት ከቤቱ አስወጣነው፤ ከደጃፉ ሆኖ ቢያንኳኳም አልከፈትንለትም፤ አላከበርነውም (የሎዶቅያን ቤተ ክርስቲያን ያስታውሷል)::

 

በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቆመን ዕንቅብ ሙሉ የሰው ዐሳብ እየነዛን፣ እያዘራን የዕንቅቡን ክፈፍ በቃሉ ሥሥ ቆዳ ብንለጉም የቃሉን ባለቤት እግዚአብሔርን ያሳዝናል። ከየጎዳናው ላገኘነው ሐሳብ መንደርደሪያ፣ ከየማድጋው ለምንቀዳው ውሃ ማጣፈጫ ብናደርገው፣ ቃሉን ሰበክነው ሳይሆን ታከክነው ማለት ይቀላል። ለቃሉ ታላቅነት ከአንገት በላይ የከንፈር አክብሮት እየቸርን በዕለት ኑሯችን ግን እያቀለልነው እንታያለን። ጽላቱን ተሸክመን ትእዛዛቱን ግን እንረግጣለን:: መምህሩም፣ ደቀ መዝሙሩም፣ ንግግሩም፣ መናገሪያውም በብዙም ይሁን በጥቂቱ ከተሰነካከለ ቆይቷል።

 

በተቃና ጐዳና ለመሄድ ከፈለግን አበሳችንን እየዘረዘርን ብቻ መዘግየት እጅግም አይረዳንም። ከሰፈሩ የተፈናቀለ፣ መንገድ የሳተ፣ አስተምህሮና የትምህርት ማኅበረ ሰብ ለመመለስ ቢሻ ቀዳሚውን የቃሉን ካርታ መዘርጋትና ማየት አለበት። የጠራውና የሰከነው ትምህርት የቱ ነው? በቃሉ የተገራው የተሞላው መምህርስ ምን ዐይነት ነው? ንጹሑን ሰማያዊ መልእክት ማቅረቢያውስ መንገድ ምንድነው? ብለን መጠየቅና ትክክለኛው መሥመር ውስጥ መግባት ያለብን አሁን ነው። 


የተሐድሶ ጥሪ:- መመርመር - መመለስ - መታደስ ከሚለው ጥናታዊጽሁፍ የተወሰደ።

Read 8042 times Last modified on Monday, 16 October 2017 09:43

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 26 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.