“የብልጽግና ወንጌል” ያለ መደበኛ እውቅና በቤተኝነት እየተስተናገደ መሆኑን የሚያመላክቱት ሐሳቦቼ በሰባት ምዕራፎች ደርጅተዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ጤንነትን፣ ሀብትን እና ስኬትን የክርስትና ዋና መልዕክት አድርጎ ላነገበው እንቅሰቃሴ፣ “ብልጽግና ወንጌል” ልከኛ ስሙ መሆኑን ከፊታውራሪያኑ አንደበት ዋቢ በማቅረብ ይሞግታል። ሐሰተኞች የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ፈተና መሆናቸውንም ያሳያል።
ሁለተኛው ምዕራፍ፣ ትምህርቱ ለምን እንደቆጠቆጠን ያስረዳል። የእንቅስቃሴውን መልዕክት ለወንጌል ባዕድ መሆኑን፣ ልጅነት ስላልሆነ ቸል መባል እንደሌለበት፣ በመገለጥ እና በተሐድሶ ስም የቀረበ ስሕተት መሆኑን ያስገነዝባል። ትምህርቱን መቃወም ሀሜት፣ ቅናት ወይም የልብ አለመስፋት እንዳልሆነ ያስረዳል። ለመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ትምህርቱ ታማኝ አለመሆኑን፣ ጽንሱ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ መሆኑን፣ አማኞችንም ለብዝበዛ ማጋለጡን ያነሳል። ትምህርቱን የምቃወምበት ምክንያት “በዘመናችን የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ ስጦታዎች የሉም፤” ወይም “ድህነትን ሀብተ ሰማይ ነው፤” በሚል መነጽር አለመሆኑን ያስገነዝባል። የጸጋ ስጦታዎች አሁንም አሉ፤ ድህነት ሀብተ ሰማይ አይደለም።
ሎሌነታቸን ለማን? የሚለው ሶስተኛው ምዕራፍ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ሚዛን መልዕክቱ ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ መሆን እንዳለበት ይሞግታል። ወንጌል “እመኑ” እንዳለን ሁሉ “አትመኑ” ብሎናልና፣ በእግዚአብሔር ስም እንካችሁ የተባልነውን ሁሉ ሳንመረምር መጋት እንደሌለብን ያሳስባል። የትምህርቱን ከምርመራ በላይ ራሳቸውን ለማድረግ “ተቀብተናልና አትንኩን” የሚሉትን ይልቁኑ አብልጠን እንድንመረምራቸው የመከላከያ ጥቅሶቻቸውን ይፈትሻል። “ከአምላክ በቀጥታ ተቀበልኳቸው” የሚባሉት ትምህርቶቹ ከዓለም አቀፍ አራማጆቹ ቃል በቃል የተቀዱ መሆናቸውን መሠረታዊ አስተምሮቶቹን በመቃኘት ያሳያል፤ ትምህርቱ በእኛው ወንጌላውያን ክርስትና ላይ ያጠላውን ጥላም ይጠቁማል። አመለካከቱ ጴንጤቆስጣዊ መባል እንደሌለበት ይሞግታል።
አራተኛው ምዕራፍ እንካችሁ የተባልናቸውን አማላይ ተስፋዎች ይቃኛል። “እምነት ካለህ ሁሉ ነገርህ ይለወጣል” የሚለውን አስተምህሮ እና ምንዳህን “አሁኑኑ” “እንደ እግዚአብሔር በማመን” ታገኘዋለህ የሚለውን አመለካከትን ይፈትሻል። የምዕራፉ ትኩረት ለውጥ ይገኝበታል የተባለው “የእምነት መንገድ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንደሌለው ማመልከት ነው። ተስፋዎችን በማሻሻጥ ሥነ ልቦናችን ላይ ጫና እያደረጉ ያሉ ምስክርነቶችም ተቃኝተዋል። ትኩረቴ “አሻሻጭ ምስክርነቶች” ከሚፈጥሩት አላስፈላጊ የጥፋተኝነት ጸጸት አማኙ እንዲድን ነው።
አምስተኛው ምዕራፍ አጋላጭ ድካሞቻችንን ያነሳል። የሥነ ሰብ ሥነ መለኮታችን ሦስትነት የሚያምን መሆኑ እና ለልምምዶች የምንሰጠው የቀዳሚነት ስፍራ ለትምህርቱ መንሠራፋት የተጫወቱትን ሚና ይቃኛል። ልምምድ ተኮር ክርስትናችንን የምንፈትሽበት የደረጀ ሥነ መለኮት አለመኖሩ፣ የሰማናቸው ልምምዶች ያልደረስንባቸው ይሆናሉ በሚል እንድናስተናግዳቸው ሰበብ መሆኑን ያነሳል።
ስድስተኛው ምዕራፍ በናሙነት በመረጥኳቸው ጥቅሶች አማካኝነት የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ አፈታት እንዴት ባለ መልኩ ለተሳሳተ ሥነ መለኮታዊ ድምዳሜ መሠረት እንደሚሆን ያመለክታል። “የብልጽግና ወንጌል” መምህራን ይደግፉናል የሚሏቸው ምንባቦች፣ እንዴት አውድ ለቀቅ ትርጉሞች እንደሆኑና፣ ያላሉትን እንዲሉ ጭቆና የተደረገባቸው መሆናቸውን ያሳያል።
ሰባተኛው ምዕራፍ ወደ ውስጥ ተመልካች እና የወደፊት አቅጣጫ ጠቋሚ ነው። “የብልጽግና ወንጌል” ጥንካሬ የአብያተ ክርስቲያናት ድካም መሆኑንን በመሞገት ራሳችንን እንድንቃኝ ይጣራል። ድህነትና ብልጽግናን አስመልክቶ ዝምታ እንደማያዋጣና ሚዛናዊ ሥነ መለኮት ብልጽግናን እና ድህነትን አስመልክቶ ካልተሰሩት ሥራዎቻችን መካከል መሆኑን ያመላክታል። መጽሐፍ ቅዱስ መበልጸግን እንደማይቃወም ያስረግጣል፤ አግዚአብሔር ለድሆች እንደሚራራ እና እንደሚሟገትላቸው ያሳያል፤ የክርስትና የብልጽግና ውዳሴ ሚዛን ትጋት ከሕይወት ንጽህና ሲጣጣም መሆኑን ያስገነዝባል፣ ብልጽግናን የሕይወት ግብ አድርጎ ማሳደድ በሚያፈርስ ጎዳና መሄድ መሆኑን በማሳየትም እንድንጠነቀቅ ይመክራል።
መጽሐፉ ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር በሚቀጥለው ቅዳሜ (ሰኔ 10፣ 2009 ዓ.ም) ቅዳሜ፣ ሰኔ 10፣ 2009 ከሰአት በኋላ ከ9 ሰዓት- 11 ሰዓት በ The Anointed Word of God Church | የተቀባ የእግዚአብሔር ቃል አገልግሎት ቤተክርስቲያን, ቦሌ ሜጋ ህንፃ ጀርባ በሚገኘው የቤተ-ክርስቲያኗ አጥቢያ ስለሚመረቅ በክብር እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡