You are here: Home

ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠራ ቤት

Written by  Friday, 15 August 2014 00:00

ቤተሰብ የየትኛውም መኅበራዊ ተቋም መነሻና መሠረት ነው። ኾኖም ከተወጠነበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ ተግዳሮቶች እንደተከበበ ይኖራል። በዘመናችንም የቤተ ሰብ ሕይወት በአጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል። በፍች፣ በሚና ቀውስ፣ በወላጆች ከቤት አለመገኘት፣ በሥልጣን መናጋት፣ ከልክ በላይ በነገሮች በመከበብ፣ በኅብረት የጋራ ጊዜ ለማሳለፍ በቂ ጊዜ በማጣት፣ በገንዘብ ችግር፣ እና በሌሎችም ባልተጠቀሱ ጕዳዮች መንሥኤ ቤተ ሰብ እየተለያየና እየተናጋ ነው። ይህ ታዲያ በቸልታ የምናየው ጕዳይ አይደለም። የአንድ ቤተ ሰብ መነካት የማኅበረ ሰብ መናጋት ነውና። የአንድ ትዳር በፍች መዘጋት ሀገርን የሚጠዘጥዝ ቍስል ሊያስከትል ይችላል። ፓት ኮንሮይ እንዳለው፣ “እያንዳንዱ ፍች፣ የአንድ አነስተኛ ሥልጣኔ መደምሰስ ነው።”

 

የቤተ ሰብ ሥምረቱም ሁለንተናዊ መቃናትን ያስከትላል። አንድ የቻይናዎች ምሳሌያዊ ንግግር አለ። “በትዳር ውስጥ መዋደድ ካለ፣ በቤት ውስጥ መጣጣምና መዋሃድ ይኖራል፤ በቤት ውስጥ መጣጣም ሲኖር፣ ባለው የሚረካ ደስተኛ ማኅበረ ሰብ ይፈጠራል፤ በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ርካታ ሲኖር ደግሞ የበለጸገ ሀገር ይኖራል። በሀገሪቱ ብልጽግና ካለም፣ በመላው ዓለም ሰላም ይሠፍናል” ይላሉ።

 

በርግጥ ቤተ ክርስቲያን ዝም ባለች ጊዜ ዓለም የእኛን፣ የልጆቻችንንና የማኅበረ ምእመናችንን ጠባይና እምነት ትቀርጻለች። ስለኾነም፣ በወደቀው ዓለም ውስጥ ሳለን እንዴት የተለወጡ የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ኾነን ለመኖር እንደ ተፈጠርን ማስተማር ይገባናል።

 

ቤተ ሰብ የተሰኘው ተቋም መለኮታዊ ምንጭና ዓላማ ያለው መኾኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በተጨማሪም፣ መጽሐፉ በቤተ ሰብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት መመሪያዎችን ይሰጠናል። ለቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮና መርሖዎች የሚኖረን እውነተኛ መታዘዝና መሰጠት የቤተ ሰብን ሕይወት ለማደስና የተናጋውን ለመጠገን ኹነኛ መፍትሔን ያመላክተናል። በዚህ ላይ ተመሥርተን ጥቂት ሐሳቦችን ቀጥሎ እናያለን።

 

የቤተ ሰብ መነሻ መሠረቱ መለኮታዊ ነው

 

ከሁሉ አስቀድሞ መገንዘብ ያለብን ይህን ነው። ገና በጠዋቱ በሥነ ፍጥረት ውስጥ የነበረውን መለኮታዊ ዓላማ ማጤን ይኖርብናል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በራሱ መልክና ምሳሌ ሠራው። “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር … እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ. 1፥26-28)። ይህ ምንኛ ታላቅ ባርኮት ነው!

 

በትዳር ውስጥ ያሉት ሁለቱ የቃል ኪዳን ተጣማሪዎች፣ ማለትም ወንድና ሴት፣ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩ ናቸው። ሁለቱም፣ ሰዎች ናቸው። የተለያዩ ባሕላዊ አስተሳሰቦች ለጾታ ልዩነት የሚሰጡት ስፍራ አሳዛኝ ቢኾንም እንኳ፣ እኛ ልንከተለው የሚገባን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት እንጂ ባሕላችንን አይደለም። ማንጓጠጥ፣ ማንኳሰስና ማስጐብደድ ከላይ በምንማራትና ከብርሃናት አባት ዘንድ በምትሰጠው ጥበብ ውስጥ አይገኙም (ያዕ. 3፥13-17)።

 

በተጨማሪ እግዚአብሔር የፈጠረው ጥምረት ልብ ሊባል ይገባዋል። በወደቀው የሰው ዝንባሌና በዐመፀኛ ምርጫዎቹ የተፈጠሩት ልምምዶች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ከመጀመሪያው አልነበሩም። እግዚአብሔር የፈጠረው “ወንድና ወንድ፣” ወይም “ሴትና ሴት፣” ወይም “ወንድና ሴቶች፣” ወይም “ሴትና ወንዶች አይደለም”፤ “ወንድና ሴት” ነው እንጂ። እግዚአብሔር “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላልና።

 

ጾታ የእግዚአብሔረው ስጦታ ነው፣ በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው። ወንድነትና ሴትነት እግዚአብሔር ኾነ ብሎ የፈጠረው ነው፤ መልካም ነው። ጾታዊ ልዩነትና ሩካቤ መልካም የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። ነገር ግን በተገቢው ንጽሕና በጋብቻ ተቋም ውስጥ ብቻ ሊፈጸም የተገባው ነው። ከዚያ ከወጣ ዐመፃና ርኩሰት ይኾናል። በአንድ ጓደኛዬ ሠርግ ላይ የተገኙ ሰባኪ ሲናገሩ እንደ ሰማሁት፣ “እግዚአብሔር የአውስቦን ፍላጎት ለመስክ አልተወውም፤ ለገበያና ለሸመታም አላሰጣውም፤ ትፍስሕቱ፣ ሰላሙና በጎ ውጤቱ የሚመጣው በትዳር ተቋም ውስጥ ብቻ ነው።”

 

እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው እያንዳንዱ ሰው በሰብኣዊ ጥምረትና መስተጋብር ብቻ ሊገኝ የሚችለውን ፍጻሜ እንዲፈልግና እንዲያገኝ በማድረግ ነው። ወንድና ሴት ኾነው የተፈጠሩት የየተጓዳኛቸውን ፍላጎት ለማሟላት ነበርና (ዘፍ. 2፥20)። ልዩ ብዙኅነትን ለመቀደስ፣ ለወዳጅነት፣ ለርስ በርስ መደጋገፍ፣ የፍቅር ፍላጎትን ለማሳካት፣ አንዱ የአንዱ አሟይ እንዲኾኑ ነው። “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” (ዘፍ. 2፥18)። ገና ከጠዋቱ የቃል ኪዳን መሥራቹ እግዚአብሔር የቤተ ሰብን መሠረት በክቡር ሐሳቡ ላይ አጽንቶታል።

 

የመጀመሪያው ቤተ ሰብ መሥራች

 

ቤተ ሰብ በመለኮታዊ ዕቅድ መጀመሩን ተመልክተናል። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት (ዘፍ. 2፥21-22)።

 

ቤተ ሰብ መለኮታዊ ዓላማ ነበረው። ቤተ ሰብን የመሠረተው እግዚአብሔር ሲኾን፣ ዓላማ ቀይሶለታል። እግዚአብሔር ለጋብቻና ለቤተ ሰብ ያቆመውን ዓላማ ተከትሎ ሕይወት ለቤተ ሰብ ምሉእነት አስፈላጊውን ሁሉ ትሰጠናለች። በፍቅር ላይ የተመሠረተ አጋራዊ ጥምረትና ወዳጅነት እግዚአብሔር በጋብቻና በቤተ ሰብ ውስጥ እንዲሠፍኑ ያቀዳቸው ዓላማዎቹ ናቸው። ይህ ኅብረት የሰው ልጅን ሕይወት የሚያጨልመውን የብቸኝነት ሠቀቀን የምንቋቋምበት ተደርጎ በእግዚአብሔር የተበረከተ ልግስና ነው። በዚህ ኅብረት ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ ክብርን ይወስዳል። “የሰው ዋነኛ መዳረሻና ግብ እግዚአብሔርን ማክበር በርሱም ብቻ ደስ መሰኘት ነውና።”

 

ጥምረቱ ክቡርና ቅዱስ ነው፤ ጽኑዕና ቡሩክ ጥምረት ነው። “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍ. 2፥24)። ጌታ ኢየሱስ ይህንኑ ሲያጸና እንዲህ ብሏል፦ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ … ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” (ማቴ. 19፥4-6)።

 

ሌላው እግዚአብሔር ለቤተ ሰብ ያለው ዓላማ ዘር (ትውልድ) መተካት ነው። “እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት” (ዘፍ. 1፥28)። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው (መዝ. 127፥3-5)። ደግሞም ክብካቤ እግዚአብሔር በቤተ ሰብ ውስጥ ያኖረው ዓላማ ነው። ይህ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ዋጋ ያለው ተግባር በቤተ ሰብ ውስጥ እንዲተገበር ቃሉ ያስተምራል። “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” (1 ጢሞ. 5፥8) ይላል። ቃሉ በሚያስተምረን መሠረት መኖር ችለን ቢኾን ኖሮ ስንት ማኅበረ ሰባዊ ቍስል ሊፈወስ በተቻለ ነበር።

 

ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሖዎች

 

መጽሐፍ ቅዱስ ለተቃናና ጤናማ የቤተ ሰባዊ ግንኙነት መለኮታዊ መርሖዎችን ያቀርባል። ተግዳሮት ሊገጥመው ቢችልም እንኳ፣ እግዚአብሔር ለቤተ ሰብ ያለው ዓላማ ሊለወጥ አይችልም። እግዚአብሔር በቃሉ የቤተ ሰብን መርሖዎች ብቻ ሳይኾን ዓላማዎቹን ለመፈጸም የሚያስችለውን ኅይሉን ጭምር ሰጥቷል።

 

መጽሐፍ ቅዱስ የጋብቻ ኅብረት የእርስ በርስ (የጋራ) መሰጣጠትና በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ መታዘዝ፣ መከባበርና መተማመን የሚገለጥበት ገጽታ እንዲኖረው ጥሪ ያደርጋል። “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ” (ኤፌ. 55፥21) በማለት። ክርስቶስ የሚከበርበት የርስ በርስ መዋደድና መከባበር የትዳር ዋልታው ነው።

 

በጋብቻ ኅብረት ውስጥ በሩካቤ ሥጋ ጥምረት የእርስ በርስ መፈቃቀድና መርካት ይኖር ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል። “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” (1 ቆሮ. 7፥3-4) ይላል።

 

አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት በኾነ የጋብቻ ኪዳን ጥምረት ውስጥ የእርስ በርስ መተማመን እንዲሠፍን ቃሉ ያዛል። ከዚያ ውጭ ያለ ፍንገጣ በሙሉ ኀጢአት ሲኾን፣ ውጤቱም አስፈሪ ነው። “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” (ዕብ. 13፥4)። ይህን እያሰብን ከማይለወጠው የዘላለም አምላክ ቃል ለእያንዳንዱ የቤተ ሰብ አባል የሚኾነውን ጥቂት እንይ። ከሚስት እንጀምር፦

 

ሚስት ምን ታድርግ?

 

ሚስት እግዚአብሔር ይመሰገን ዘንድ ባሏን ትውደደው። “ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ … እንዲሆኑ” (ቲቶ. 2፥3-5) ታዘዋል። ያለመውደድ መታዘዝ የለምና።

 

ሌላው ለአመራሩ ፈቃደኛ ምላሽና መታዘዝ መስጠት አለባት። “ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ” (ኤፌ. 5፥22-24)።

 

ሚስቶች (ያመኑም ኾነ ያላመኑ ባሎች ቢኖሯቸው) የባሎቻቸውን አመራር እንዲቀበሉ እግዚአብሔር ያዛቸዋል። “እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው”(1 ጴጥ. 3፥1-2) ይላል።

 

ምንባቡ እንደሚያመለክተን የሚስቶች ምሳሌያዊ ኑሮ የማያምኑ ባሎቻቸው ክርስቶስን እንዲያውቁ ምክንያት ሊኾናቸው ይችላል። በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ሌላውን ከመውቀሱም በላይ፣ ወንጌልን ለማካፈል መደላድል ይፈጥራል። ነገር ግን ይህ ምንባብ አንዲት አማኝ ሚስት እምነቷን እንድታስተባብል ወይም እንድታመቻምች ከማያምን ባሏ ተጽዕኖ ቢደርስባት እምነቷን ለመተው እንድትታዘዘው አይፈቅድም። በተጨማሪም ሚስቲቱ ባሏን ታክብረው ተብሏል (ኤፌ. 5፥33)።

 

ባልስ ምን ማድረግ አለበት?

 

ባልማ ሚስቱን ሊወድዳት ይገባዋል። እንዴት ባለ ፍቅር ይውደዳት? ምላሹ አስደናቂ ነው። “ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ … እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። … ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት” (ኤፌ. 5፥25፡28፡33)።

 

ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ራሱን በሚወድበት ልክ ማስፋት አለበት። ባሎች ሚስቶቻችንን ለመውደዳችን ማሳያዎችን እየቈጠርን መንቀባረር አንችልም። ንጽጽሩ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የወደደበትን ያህል ነውና። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ስለ ወደዳት ሞተላት። እኛስ? ጥሪያችን ሕይወትን እስከ መስጠት ድረስ መውደድ ነው። አንዳንዶቻችን ፍቅራችንን በሥራ መግለጥ ይቅርና፣ በቃላት አውጥተን መናገሩ እንኳ ይከብደናል። “እወድሻለሁ” የሚለው ቃል በጕረሮ ላይ እንደተሠነቀረ አጥንት የሚተናነቃቸው አሉ። እንናገረው። ጆርጅ ኤሊየት፣ “እኔ የምሻው መወደድን ብቻ አይደለም። ይልቁንስ ተወዳጅ መኾኔ እንዲነገረኝም እፈልጋለሁ። የዝምታ ክበቡ ከመቃብር የበለጠ የሰፋ ነውና” ትላለች። እውነቷን ነው። በርግጥ መውደድ ከቃላት በላይ ነው፤ ራስን መስጠት ድረስ ይዘረጋልና።

 

በተጨማሪም ባል ለሚስቱ ሁለንተናውን መስጠት ይኖርበታል። “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ኤፌ. 5፥31)። ይህም ብቻ አይደለም። ሊረዳት ድካሟንና ያለችበትን ኹኔታ ሊገነዘብ ይገባዋል። ፍቅር ሲቀበሉት ሳይኾን ሲሰጡት ይሠፋል። ደግሞም፣ የሕይወትን ተስፋ እንደምትቀበል ዐውቆ ሊያከብራት ይገባዋል። “እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው” (1 ጴጥ. 3፥7)።

 

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊኖራቸው የሚገባ ኀላፊነት

 

“እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው” (ዘዳ. 6፥6-7)። ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ኀላፊነት አለባቸው። እያንዳንዳችን የቤታችን ካህን ነን። እኛ ካላስተማርናቸው ልጆቻችንን ማን እንዲያቀናልን ነው የምንጠብቀው? የልጆች የመጀመሪያና ትልቁ ዓለማቸው ቤታቸው ነው። “ነገሥታቱም” ወላጆቻቸው ናቸው። በንጉሥ እጅ ከሚገኘው በትረ መንግሥት ይልቅ በእናት እጅ ውስጥ የላቀ ኃይል አለ። ቢሊ ሰንዴይ በወለጆች እጅ እግዚአብሔር ስላስቀመጠው የባለ አደራነት ጸጋ ሲናገር፣ “በፈሪሃ እግዚአብሔርና በመንፈሳዊነቷ ከታወቀች እናት ክንዶች መኻል ልጅን ፈልቅቆ ለማውጣት የሚቻላቸው በቂ አጋንንት በሲኦል ውስጥ ይኖራሉ ብዬ ማመን ይቸግረኛል” ይል ነበር። ወላጆች ልጆቻቸውን ማሠልጠን ይኖርባቸዋል ማለት ነው። “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” (ምሳ. 22፥6).

 

ታዲያ ልጆች ፍቅርና ክብካቤ የታከለበት ሥነ ሥርዓታዊ አስተዳደግ እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለብንም። “እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” (ኤፌ. 6፥4)። ሥልጠና በመቀጥቀጥና በማፍጠጥ የሚመጣ አይደለም። ተግሣጻችንና ቅጣታችን እንኳ የልጆቻችንን ባሕርይ ማቅኛ መሣሪያ እንጂ የንዴት ማብረጃ መኾን የለበትም። ቫለሪ ቤል “ከልጆችህ ዐይኖች ፊት ጠፍተህ በልባቸው ቦታ አግኝ” በተባለው ሥራው እንዳሰፈረው፦ “ልጆችህ በዙሪያህ ባሉ ገዜ ሁሉ ዐይኖችህ ብርሃን ይርጩ። ጨምረህ፣ ጨምረህ ሣቅ። እነርሱ በአንተ ዘንድ ባይኖሩ ኖሮ ምን ያህል ባዶነትና ሠቀቀን የሞላው ጸጥታ ይጋርድህ እንደነበር ንገራቸው። ወደ ሕይወትህ በሚያመጡት ነገሮች ሁሉ ደስ ይበልህ። የሚያከናውኑትን ነገር ሁሉ በጥሞና ተከታተልላቸው። ይህን ስታደርግ ግን የወላጆች ግዴታን ለመወጣት ብለህ ሳይኾን፣ ሙሉ ለሙሉ ራስህን በደስታ አሳትፈህ መኾን ይኖርበታል።”

 

በተጨማሪ ልጆች አግባብ ያለው ምሳሌነትን የሚያሳያቸው አርአያ እንደሚፈልጉ አትርሱ። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ፣ “…በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፤ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ” (2 ጢሞ. 1፥5) ብሎታል። ሦስት ትውልድ የተላለፈ እምነት ነበር። ልጆቻችሁ እናንተ የሄዳችሁበትን መንገድ ዙሩን አክርረው ዕጥፍ በዕጥፍ ነው የሚከንፉበት። እኛ የማናደርገውን መልካም ነገር ከልጆቻችን መጠበቅ አንችልም። ያልዘራነውን ለማጨድ መጠበቅ የዋህነት ነው።

 

አባቴ የነገረኝ አንድ ታሪክ አለ። “ሰው ምን ይለኛል?” ብሎ አባቱ ባረጀ ጊዜ ለመጦር ወደ ቤቱ ያመጣ አንድ ገበሬ ነበረ። ይህ ገበሬ ሰው ግን አረጋዊውን አባቱን ዝንጀሮ እንዲጠብቅ በገደል አፋፍ ላይ በየማለዳው እያስቀመጠው ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር። ያም ሽማግሌ በርሃብ፣ በቍርና በሐሩር እየተጠበሰ ኖሮ ሞተ። ከዓመታት በኋላ ይህ ልጅ ተራ ደረሰውና አባት ኾነ፤ ሸመገለናም በራሱ ልጅ የመጦር ተራ ደረሰው። የርሱም ልጅ በተመሳሳይ መንገድ ከፈፋ ላይ እየወሰደ ሰብሉን ከዝንጀሮ እንዲጠብቅ ያመላልሰው ጀመር። አንድ ቀን ግን ባለበት ቦታ እንቅልፍ ጥሎት ኖሮ ዝንጀሮ ሰብሉን ክፉኛ አጠፋ። በዚህም የተናደደው ልጁ ከገደል ሊጨምረው ሲጎትተው፣ ራሱ ባባቱ ላይ ሲያደርስ የኖረው ግፍ ሁሉ ታሰበውና “ተው ልጄ፣ ተው፤ በአባቴ ላይ የከፋሁበት ብኾንም እንኳ ከዚህች ቦታ አላሳለፍኩትም ነበር” ሲል ተማጸነ። የዘሩት መብቀሉ አይቀርም።

 

ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሊኖራቸው የሚገባ ግንኙነት

 

ልጆች ወላጆቻቸውን ማክበር ይገባቸዋል። የተስፋ ቃል ያለት ፊተኛ ትዕዛዝ አለች። “አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም” (ዘጸ. 20፥12) ትላለች። ዕድሜኣችንን ለማርዘም በማለት የምናሳድደውን ሰላጣ ያህል ይህን ትዕዛዝ ምን ያህል አክብረነው ይኾን ያሰኛል?

 

ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ ይጠበቅባቸዋል። አማራጭ ሳይኾን የሚገባ ነው። “ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና።” (ኤፌ. 6፥1)። ደግሞም ጌታን ያስደስተዋል። “ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላ. 3፥20)። በተጨማሪም፣ ልጆች ከወላጆቻቸው መማር ይኖርባቸዋል። “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናንትህንም ሕግ አትተው” (ምሳ. 1፥8)።

 

ልጆች ዐቅማቸው ለደከመና ራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ወላጆቻቸው ድጋፍ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው። “ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና” (1 ጢሞ. 5፥4) ተብሎ ተጽፏል።

 

መደምደሚያ

 

መጽሐፍ ቅዱሳችን በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ጤናማ፣ ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት ለመቀዳጀት የሚረዳንን መመሪያዎች ይዟል። ክርስቲያኖች ስለ ቤተ ሰብ ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን በማስተዋልና በአንክሮ በመተግበር የእግዚአብሔርን በረከት እየተካፈሉ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲኖሩ ይገባቸዋል።

 

ማኤ ዌስት የተባሉ ሰው፣ “ፍቅር እውር … ትዳርም ተቋም ነው ሲሉ እሰማለሁ። መልካም ነው፤ ይሁን እንጂ እስካሁን የዕውራን ብቻ ከመኾን ባልተላቀቀ ተቋም ውስጥ ለመግባት አልተዘጋጀሁም” ሲሉ ተሣልቀዋል። በርግጥ ፍቅር ዕውር አይደለም። ምሕረትና ራስን መካድ የተሞላ የመታዘዝ ታማኝነት እንጂ። ስለዚህ ባልና ሚስት ርስ በርስ በመሰጣጠትና በመተማመን ትዳራቸውን መምራት ይኖርባቸቸዋል።

 

ትዳር ሁለት ፍጹማን ሰዎች የተገናኙበት ተቋም አይደለም። ሁለት ደካማ ሰዎች በእግዚአብሔር ጸጋ በርትተው ርስ በርስ እየተደጋገፉ የሚያድጉበት ኅብረት ነው እንጂ። ዴቭ ሙረ፣ “ጋብቻ ታላቅ የሚኾነው ሁለት ፍጹም ሰዎች በጋራ ሲገናኙበት ሳይኾን፣ ሁለት ፍጹማን ያልኾኑ ሰዎች በልዩነቶቻቸው መደሰት በሚችሉበት ጊዜ ነው” እንዳለው ነው።

 

ሁላችንም ስለ ትዳር በነበሩን የልጅነት ሕልሞቻችን ውስጥ ፍቅር እስካለ ድረስ ትዳር እንደ ሐር ክር ለሰስ ብሎ የሚጓዝ ይመስለን ነበር። ነገር ግን ትዳር ብዙ ምክክር፣ መተሳሰብ፣ ማመቻመችና ጥምረት የሚጠይቅ ነው። በትዳር ውስጥ እያንዳንዱ ተጣማሪ ሐያሲ ሳይኾን አበረታች፣ በደልን የሚቈጥር በመኾን ፈንታ ይቅር ባይ የመኾንን ጥበብ መማር አለበት። በጋብቻ ውስጥ ያለው ውበት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው ፍቅርና ርኅራኄ አዕማዶቹ ሲኾኑ ነው።

 

እውነተኛ የትዳር አጋር ይሰማል፣ ያዳምጣል፣ ይመከራል፣ ሌላ መንገድ ሊኖር መቻሉንም ይገነዘባል። ሁሉን ነገር በመዶሻ ብቻ ለመሥራት እንደሚሞክር አናጢ አትሁኑ። በትዳር ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ “ምስማር” አይደሉም። ከክስ ይልቅ ማበረታታት፣ በደልን ከመቊጠር ይልቅ መቻቻልና መተውን ማወቅ፣ በተለይም ይቅር ማለት አስፈላጊ ነው። እርቀ ሰላም ከሐቅ ጋር መጋጠም ነው። ሁሉን ነገር በመገፍተርና በውሳኔ ብቻ አናስተካክለውም። ይቅር ካልተባባልንና የአጋራችንን ፊት ማየት ካልቻልን የግዚአብሔርን ፊትም ማየት አንችልም (ማቴ 18፥35)።

 

ቤተ ሰብ የተባለው ተቋም ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠራ ነው። “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ። እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል” (መዝ. 127፥1)። ይህ ቃል ያለ እግዚአብሔር ሊሠራ የሚሞከርን ቤት ፍሬ ቢስነት ነው የሚናገረው። “እግዚአብሔር ብቻ ይሠራዋልና፣ እናንተ ዝም ብላችሁ እዩ” አይልም። “ከእግዚአብሔር ጋር ዐብራችሁ ሥሩ ነው” የሚለው። ያላችሁን ሁሉ በትዳራችሁ ላይ የበለጠ ባዋላችሁ መጠን፣ ትዳራችሁ የበለጠ ዋጋ ያለው እየኾነ ይመጣል። መውደቅ መነሣት ቢገጥማችሁ እንኳ፣ ነገ ሌላ ቀን ነው፤ የአምላካችሁ በጎነቱ ብሩህ የድል ማለዳን ያመጣላችኋል። ሮጀር ባብሰን። “ይህን አንድ ነገር አትርሱ፤ የመጨረሻው ስኬትም ይሁን የመጨረሻው ውድቀት የገጠመው ሰው የለም። የደረሳችሁበት ሽንፈትም ይሁን ስኬት የመጨረሻው አይደለም” እንዳለው ነው። በርቱ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠሩ አይወድቁም። በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅሙ የለምን (መዝ. 126፥5)? መዝሙረኛው እንዳለው፣ “ቊጣው ለዐጭር ጊዜ ነው፤ ቸርነቱ ግን እስከ ዕድሜ ልክ ነውና፤ ሌሊቱን በልቅሶ ቢታደርም፣ በማለዳ ደስታ ይመጣል” (መዝ. 30፥5 ዐመት)። እግዚአብሔር ትዳራችሁን ይባርክ።

Read 58737 times Last modified on Tuesday, 19 August 2014 14:08
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Most Read

ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠራ...

Written bySolomon Abebe Gebremedhin

It is Okay not t...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

Lust On a Driver...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

የአገር ያለህ!...

Written byNegussie Bulcha

 

 

 

.

Right Now

We have 16 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.